የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በ2017 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

Jul 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ከቡና የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ በተከናወኑ የለውጥ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡንም ባለሥልጣኑ ገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ በ2017 በጀት ዓመት 326 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት በእቅድ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ 470 ሺህ ቶን የሚጠጋ ምርት ወደ ውጭ መላኩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህም 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

የተገኘው ገቢ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርጋት መሆኑን ጠቅሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሦስተኛዋ ቡና አምራችና ላኪ አገር የሚያደርጋት መሆኑንም አብራርተዋል።

ከቡና የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው፤ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብልጫ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ከቡናው ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የፖሊሲ ሪፎርም መደረጉን ጠቁመው፤ በዚህም አርሶ አደሮች ቡናን በቀጥታ ለውጭ የሚያቀርቡበት ሥርዓት መመቻቸቱን ጠቅሰዋል።

ለአርሶ አደሮች ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች መሰጠቱ፣ ያረጁ ቡናዎች እንዲጎነደሉ መደረጉ እንዲሁም አዳዲስ ዝርያ ያላቸው ቡና ተክሎች መተከላቸው ምርቱ እንዲጨምር ማድረጉንም ተናግረዋል።

የቡና አቅራቢዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ዋጋ ላይ ያላቸው የመደራደር አቅም ከፍ እንዲል መደረጉም ከቡና የሚገኘው ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

እንደ ዶክተር አዱኛ ገለጻ የቡና ምርት ጥራት ቁጥጥር ተግባራትን በማከናወን የተሻሻሉ ደረጃ ያላቸው የቡና ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።

በዚህም አርሶ አደሮችና የቡና አቅራቢዎች ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት በርካታ የቡና ችግኞች መተከሉን ጠቁመው፤ ይህም የቡና ምርት እንዲጨምር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉን ገልጸው በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ግብ መያዙን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.