የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የክልሉ መንግስት ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

Jul 8, 2025

IDOPRESS

አዳማ፤ሰኔ 30/2017 (ኢዜአ):- የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ ስራዎች ላይ በማተኮር እየሰራ መሆኑን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለፁ።

በአዳማ ከተማ አስተዳደር 171 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።


ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የዶሮና የወተት ላሞች እርባታ ማዕከላት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የአዳማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህንፃና የአስተዳደር ህንፃዎች፣ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያና መልሶ መጠቀሚያ ማዕከል፣ የመኖ ማቀነባበሪያ እንዲሁም የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ፤ ''የማንሰራራት ዘመን ላይ ሆነን የማይቻሉ የሚመስሉ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን እያደረግን ነው'' ብለዋል።


የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ ፍጥነትና ጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ መንግስት የህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ ልዩ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት ከማድረግ ባለፈ አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ስራ ጎን ለጎን እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


በበጀት ዓመቱም የክልሉን ህዝብ፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ አጋር አካላትን ጨምሮ የመንግስትን አቅም አንድ ላይ በማቀናጀትና በመጠቀም ስፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

አሁን እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ርብርብ ይቀጥላልም ብለዋል።


የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

''በከተማዋ የተቀመጠውን የልማት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል'' ያሉት ከንቲባው በከተማዋ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በተመሳሳይም በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ዘዴ በመደገፍ በአብዛኛው ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም 122 አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ ከ30 በላይ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አክለዋል።

ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶችም በህዝብ ተሳትፎ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በየደረጃው ባለው የአስተዳድሩ መዋቅር ጥረት የተገነቡ መሆናቸውን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.