የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው-ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

Jun 9, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡


የገንዘብ ሚኒስትሩ ወቅታዊ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ጉዳዮችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


በማብራሪያቸውም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችል አበረታች ሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡


በተያዘው በጀት ዓመት ሐምሌ ወር ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በቂ ዝግጅት ተደርጎ በመተግበሩ በሁሉም ዘርፎች ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡


የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲተመን መደረጉ፣ የፊስካል ፖሊሲና አዲስ የገንዘብ ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረጋቸው፣ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡


የምንዛሪ ግብይቱ በተረጋጋ መልኩ እየቀጠለ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበት ዓመት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዚህ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡


በሌላ መልኩም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ የገቢ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቁመው፤ማሻሻያው የዋጋ ግሽበት ዝቅ እንዲል ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡


ሁሉም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ- ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የሌሎችም አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግም በኢኮኖሚው የሚደርጉት አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲጎለብት መከታተል ብሎም ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ አመርቂ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ረገድ ትልቅ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


በተያዘው በጀት ዓመት መንግስት ከፍተኛ የበጀት ድጎማ ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህም የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በገበያ በመወሰኑ ምክንያት ሊፈጠር የነበረውን ጫና መቋቋም ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡


ለአብነትም በነዳጅ፣ በማዳበሪያ፣ በዘይትና ስኳር እንዲሁም መሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ በሌሎችም ድጎማ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ከ10 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ለሚገኘው የከተማና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ወደ 60 ቢሊዮን ብር በመመደብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡


በቀጣይም በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.