ሀዋሳ፤ ግንቦት 29/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር በዓሣ ሀብት ልማት ላይ እመርታዊ እድገት ማስመዝገቡን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በሲዳማ ክልል እየተከናወነ ያለውን የዓሣ ሀብት ልማት ሥራ ተመልክተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ፋሲል ዳዊት በወቅቱ እንደገለጹት ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በዓሣ ሀብት ልማት ላይ እመርታዊ እድገት ተመዝግቧል።
ከሌማት ትሩፋት ትግበራ አስቀድሞ እንደሀገር የዓሣ ሀብት ልማት ሥራው በዋናነት ተፈጥሯዊ በሆኑ የውሃ አካላት ላይ በማተኮር ይከናወን እንደነበር አስታውሰው በመርሀ ግብሩ አማካኝነት በአርሶ አደር ማሳ ላይ በሚዘጋጁ ኩሬዎች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ አርሶ አደሮች የዓሣ ሀብት ልማቱን በኩታ ገጠም እያካሄዱ እንደሚገኙና ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ፋሲል አክለውም ከዚህ በፊት በዓሣ ጫጩትና አይነት እንዲሁም በዓሣ መኖና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ የነበሩ ችግሮችን በመፍታ አቅርቦቱን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ሲጀመር የነበረው ዓመታዊ የዓሣ ጫጩት ምርት በመቶ ሺዎች ይቆጠር እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ቁጥሩን ከስምንት ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋ፡፡
ይህም በህብረተሰቡ ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም በምግብና ሥነ-ምግብ ሥርዐት ላይ መሻሻሎችን እያመጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አደገ አለሙ በክልሉ በዓሣ ሀብት ምርትና አጠቃቀም ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ሰፊ የአመለካከት ለውጥ ማማጣት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በተለይ ለኩሬ ዝግጅት የሚሆን ውሃ በማሳቸው ማግኘት የሚችሉ አርሶ አደሮች ኩሬዎችን በማዘጋጀት በስፋት ወደ ዓሣ እርባታ እየገቡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ግብዓት የሚሆኑ የዓሣ ጫጩቶችን ለማምረት ቢሮው በሁለት የዝርያ ማባዣ ማዕከላት የደጋና የቆላ ዓሣ ዝርያዎችን በማራባት ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ ኩሬዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ከታቀደው 175ሺህ የዓሣ ጫጩቶች 136 ሺህ ጫጩቶችን ማሰራጨት እንደተቻለና ቀሪዎቹን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰራጩ አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ዳሌ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው ዓሣን በኩሬ ከሚያራቡ ወጣቶች መካከል ደርቤ ሹሜ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለአስር በመሆን በስድስት ኩሬ ላይ ዓሣ ማርባት መጀመራቸውን ጠቅሶ እስካሁን አራት ጊዜ ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግሯል፡፡
የራሳቸውን የዓሣ ምግብ ቤት በመክፈትም ጥሬ ዓሣ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጾ በሥራቸው ውጤታማ በመሆን ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በሁላ ወረዳ በኩታ ገጠም የዓሣ ልማት እያከናወኑ የሚገኙት አርሶ አደር ታደሰ በኬ የመንደሩ አርሶ አደሮች በሌሎች አካባቢ ያሉ ዓሣ አርቢዎችን ውጤታማነት በማየት ወደ ሥራው መግባታቸውን ገልፀው አሳ እርባታውን እያሰፉ መሆናቸውን ተናግረዋል
በምልከታው ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲሁም ከክልል ቢሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025