አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ የዓለም የፋይናንስ ስርዓት የአፍሪካን ነባራዊ ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ ማሻሻያዎች ሊደረግበት እንደሚገባ የአፍሪካ ኤክስፖርት እና ኢምፖርት ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ተጠባባቂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኤሪክ ኢንቶንግ ሞንቹ ገለጹ።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርሳቸውና ከተቀረው ዓለም ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ የማሳደግ ስራዎች እንዲሁም ግዙፍ አህጉራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን እየደገፈ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተቋሙ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር የያዘው ግብ ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ጋር የተጣጣመ መሆኑንም አመልክተዋል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ሴክሬተሪያት እና አፍሪኤግዚም ባንክ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ሁለቱ ወገኖች የነጻ ንግድ ቀጣናው ትግበራ ውጤታማ እንዲሆን በትብብር እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
ባንኩ በስምምነት ማዕቀፉ አማካኝነት ጨርቃጨርቅና አውቶሞቲቭን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የምርት ጥራት ደረጃዎች ወጥነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በቀጣይም ባንኩ የነዳጅ ምርቶች ዘርፍ ተመሳሳይ ጥራት እንዲኖራቸው የሚያስችል ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ባንኩ የአፍሪካን ኢንዱስትሪ ልማት ለማጠናከርና የወጪ ንግድን ለመጨመር እያደረገ ያለው ድጋፍ ከንግድ ቀጣናው ስምምነት ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።
ከአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን በባንክ መተማመኛ ሰነድ(ሌተር ኦፍ ክሬዲት) አማካኝነት ሀገራት ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱን መተገበር የሚያስችላቸውን ገንዘብ በብድር እያቀረበ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
በሌላ በኩል ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት እንዲቀየር በአፍሪካ ሀገራት እየቀረበ ያለው ጥያቄ ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከአፍሪካ ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ባከበረ ሁኔታ በትብብር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የፋይናንስ ተቋማቱ በአፍሪካ ሀገራት የህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች የፀደቁ የአፍሪካን የንግድ ህግ ስምምነቶችን ያለመቀበል ፍላጎት ሉዓላዊነትን የሚጥስ ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት ከአፍሪካ ህልሞች እና ራዕዮች እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያ ሊደርግበት ይገባል ነው ያሉት።
ከፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ ውጪ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው መምራት እና ማስተዳደር የሚያስችላቸውን ስራዎች ማከናወን እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የአፍሪካ የብድር ምዘና ኤጀንሲ(AfCRA) መቋቋም መልካም ጅማሮ እንደሆነና መሰል ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
እ.አ.አ 1993 የተመሰረተው አፍሪኤግዚም ባንክ የአፍሪካ የባለብዝሃ ወገን የፋይናንስ ተቋም ነው።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025