የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በተለያዩ ሐይቆች ላይ በዘመናዊ ጀልባዎች የታገዘ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው

Jun 5, 2025

IDOPRESS

ጅማ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ በተለያዩ ሐይቆች ላይ በዘመናዊ ጀልባዎች የታገዘ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ገለጸ።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) እንዳሉት ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የሀገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርት እንዲኖር እየተሰራ ነው።

ለዚህም የሚያግዙ ዘመናዊ ጀልባዎችን በማስመጣት በሀገር ውስጥ ሐይቆች ላይ ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ 'ጣና ነሽ 2' ለዚሁ አገልግሎት ወደ መዳረሻዋ ባህር ዳር እየተጓጓዘች መሆኑን ተናግረዋል።

ጀልባዋ 188 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳላትና ይህም ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በቀጣይም እንደ 'ጣና ነሽ 2' አይነት ዘመናዊ ጀልባዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የሀገር ውስጥ የውኃ ትራንስፖርትን በማሻሻል የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

ላንጋኖ እና ሻላን ጨምሮ በሁሉም ሐይቆች ላይ በዘመናዊ ጀልባዎች የታገዘ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በዓለም ላይ የመዳረሻ ወደቦችን ብዛት ወደ 350 ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የጭነት አቅምም ከፍ እንዲል ይደረጋል ብለዋል።

ከገቢ አንጻርም በዘጠኝ ወር አፈጻጸም የተሻለ ገቢ መገኘቱን ገልጸው፣ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተቋሙን ከማንዋል አሰራር በማላቀቅ የዲጂታላይዜሽን አሰራር እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው ይህም ወጪን ከመቆጠብና ገቢን ከመጨመር ባለፈ ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በጅማ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያደሰውን መኖሪያ ቤት ለነዋሪዎች ማስረከቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.