የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን የማጠናከርና የማበረታታት ተግባር እየተከናወነ ነው-ቢሮው

May 16, 2025

IDOPRESS

ወልቂጤ፤ግንቦት 7/2017 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን የማጠናከር፣የማበረታታትና የማሸጋገር ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለጸ።


በክልሉ ጉራጌ ዞን ለ4ኛ ዙር የተዘጋጀው የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ውድድር በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።


በወቅቱም የቢሮው ምክትልና የፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን እንዳሉት፥ በክልሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች የማጠናከርና የማበረታታት እንዲሁም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስና ለማሸጋገር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።


ለዚህም ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በየአካባቢው የፈጠራ ስራዎች ውድድርና ኤግዚቢሽኖች በማዘጋጀት እንዲተዋወቁ ከማድረግ ባለፈ በዘርፉ የተሰማሩትን በግብዓትና በክህሎት ስልጠና የመደገፍና የማበረታታት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


የፈጠራ ስራዎቹ የማህበረሰብን ችግር የሚፈቱ የስራ እድል የሚፈጥሩና በተጓዳኝ ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች የሚያስቀሩ እንዲሁም ምርታማነት እንዲጨምርና ዘላቂ ዕድገት እንዲመዘገብ ጉልህ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።


የጉራጌ ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በፈጠራ ስራዎቹ ላይ የሚሳተፉ አካላት ተገቢው ድጋፍ ተሰጥቷቸው ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


በውድድሩ 95 የፈጠራ ስራዎች የቀረቡ ሲሆን ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች መገኘታቸውንና ለአሸናፊዎች ዕውቅና የመስጠትና የማበረታታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ባሻገር የፈጠራ ክህሎት ያላቸውና በዘርፉ ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁበት እንዲሆኑ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም ናቸው።


በጉራጌ ዞን በእኖር ወረዳ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው እሱባለው ተክለወልድ የግብርና ስራን ለማዘመን የሚያስችሉ የፈጠራ ውጤቶችን በመፍጠር በኤግዚቢሽኑ ላይ ማሳየቱን ገልጿል።


የድንችና መሰል የስራ ስር ሰብሎች ምርት መንቀያ ማሽንን በፈጠራ ስራው ያሳየው ደግሞ በጉመር ወረዳ የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ታደሰ ክፍሌ ነው።


ይህም ጉልበት፣ጊዜን እና ገንዘብን ከመቆጠብ ባለፈ ብክነት እና የምርት ብልሽትን የሚያስቀር ነው ብሏል።


ሌላኛው የፈጠራ ባለሙያ ተማሪ አብድልሃፊዝ ፀጋዬ በሙህር አክሊል ወረዳ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን የእሳት አደጋን እና ወንጀልን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር መፍጠሩን ጠቁሟል።


እነዚህንም ከአካባቢ በሚገኙ ቁሳቁስ ሰርቶ በቀላሉ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ የሚቻሉ ናቸው ብሏል።


የጉታዘር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንግሊዝኛ መምህር ስንታየሁ ክፍሌ ደግሞ ኤሌክትሪክ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች በአነስተኛ የሶላር ኃይል ፕላዝማ እና ቴሌቪዥን ማንቀሳቀስ የሚችል፣ሞባይል ቻርጅ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መፍጠሩን ተናግሯል።


ይህም በአንድ ማእከል የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችልም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.