የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የግብርና ስርዓት ሽግግር በአገር በቀል እውቀት፣ልማድና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እውን ሊሆን ይገባል

Jul 30, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 22/2017 (ኢዜአ)፦የግብርና ስርዓት ሽግግር በአገር በቀል እውቀት፣ልማድና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እውን ሊሆን እንደሚገባ በጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ትብብርና የምግብ ዋስትና ልዩ መልዕክተኛ ስቴፋኖ ጋቲ ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የተመድ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በመዝጊያ መርሃግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ትብብርና የምግብ ዋስትና ልዩ መልዕክተኛ ስቴፋኖ ጋቲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲረጋገጥና የምግብ ስርዓት ሽግግር እውን እንዲሆን እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል፡፡

ድርጅቱ የጀመረው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡


የምግብ ሽግግር ስርዓቱ የማይበገር፣ሉዓላዊነትን ያከበረና ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን ጠንካራ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በጉባዔው የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል ሁላችንም በጋራ ወደፊት መጓዝ አለብን ብለዋል፡፡

ጉባዔው ስሜታችንን ከማንጸባረቅ ባለፈ በፖለቲካ ቁርጠኝነት በመታገዝ ተግባራዊ ለውጥ ለማምጣት የምንተጋበት ነው ብለዋል፡፡

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ፣በተለዋዋጭ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ፣ በሸቀጦች ዋጋ መናርና በተለያዩ ቀውሶች እየተጠቃች በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ማሻሻል የልማት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊነትን ማስጠበቅና ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

የጋራ የሆነ ነጋችንን እውን ለማድረግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ስትራቴጂያችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከአፍሪካ ጋር በግብርና ዘርፍ አብረን ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን ቀድመን አረጋግጠናል፣ ለዚህ ደግሞ የጋራ ኢኒሸቲቭ ተግባራዊ በማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የተጀመሩ ፕሮግራሞችን ደረጃ ከፍ ማድረግ፣ አዳዲሰ አጋርነት መመስረት እና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት፡፡

ጣሊያን የምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥን አጥብቃ እንደምታከብር የገለጹት ስቴፋኖ ጋቲ ተግባሩ እውን የሚሆነው በሁሉም አገራት የጋራ ጥረት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

የግብርና ስርዓት ሽግግር በአገር በቀል እውቀት፣ልማድና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እውን ሊሆን እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ጣሊያን አገራት አቅማቸውን ተጠቅመው የማይበገር የግብርና ስርዓት እውን እንዲያደርጉ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ነው ያረጋገጡት፡፡

የግብርና ስርዓት ሽግግር በፖሊሲ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ላይ ተመስርቶ የሚረጋገጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ለሽግግሩ መንግስታት፣ የግል ባለሃብቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.