አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ጤናው የተጠበቀ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የምግብና ስርዓተ-ምግብ ፖሊሲዋን በጥናትና ምርምር ደግፋ እየሰራች ነው።
ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ በሚካሔደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ-ምግብ ጉባኤ ኢትዮጵያ በስርዓተ - ምግብ ሽግግር ያላትን ተሞክሮ ታቀርባለች።
የኢትዮጵያ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ፖሊሲ ቀጣይነት ያለው፣ ደህንነቱ የተረጋገጠና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ላለፉት ሰባት ዓመታት በትግበራ ላይ ይገኛል።
የፖሊሲውን ዓላማ ለማሳካትና በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት ከጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክተር አልጋነሽ ቶላ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ጤነኛና አምራች ዜጋ መፍጠር የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራች ሲሆን የህብረተሰቡን የአመጋገብ ስርዓት ለመቀየር የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ውጤቶች እየወጡ ይገኛሉ።
የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት አምራችና በአዕምሮ የጎለበቱ እንዲሆኑ በመቀንጨርና መቀጨጭ ላይ ትኩረት ያደረጉ የህጻናት ምግብን የሚያዳብሩ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለእናቶችና የበሽታ መከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጨማሪ ምግቦችን ማግኘት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
አምራችና ጤነኛ ዜጋ ለመፍጠር በምርት ሂደት ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ እንዲመረትም የፖሊሲ ግብዓት መስጠት ተቋሙ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
ከአርሶ አደሮች፣ ምርት አቅራቢዎች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች የምግብና ስነ-ምግብ ተዋናዮች ጋርም በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቀጣይነት ያለው፣ ደህንነቱ የተረጋገጠና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ላለው የኢትዮጵያ የምግብና ስርዓተ-ምግብ ፖሊሲ ስኬት የምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ስርዓተ- ምግብ(Food System) የምግብ ማምረት፣ ማቀነባበር፣ ማሰራጨት፣ መጠቀም እና ማስወገድ ውስጥ ያሉ ሂደቶችና ተግባራትን አጠቃሎ የያዘ ሀሳብ ነው።
የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ ጥናትና ምርምር፣ የከባቢ አየር ሁኔታ እንዲሁም ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን በስርዓተ ምግብ ውስጥ ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው።
ስርዓተ- ምግብ ሁለንተናዊ እና ሁሉን አቀፍ መሆኑ በኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች የምግብ ስርዓት የሽግግር ጉዞ እውን እንዲሆን ትልቅ ጠቀሜታም አለው።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025