ሰቆጣ፤ሐምሌ 18/2017(ኢዜአ)፡- የመስቀሎዋ ግቢው መንደር "የነባር ደኖች ባለጸጋ፤ የአረንጓዴ ልማት መገለጫ"
"ግቢው መንደር" ከርቀት ሲመለከቷትእድሜ ጠገብና አዳዲስ የለሙ ደኖችን የያዘች በልምላሜዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታወቀች የመጣች፤ አርዓያነቷም እየገነነ የመጣ ትንሽዬ መንደር ናት።
የእድሜ ጠገብ ደን ባለቤትና የአዳዲስ ደን ልማት መገለጫ የሆነችው "ግቢው መንደር" የምትገኘው ዝናብ አጠር በሆነውና የተራቆተ ተራራ አግጦ በሚታይበት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በጋዝጊብላ ወረዳ መስቀሎ ቀበሌ ነው።
ግቢው መንደር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትልቁ ተራራ በሆነው ቤላ ተራራ ስር ከተመሰረቱ መንደሮች አንዷ ናት።
ግቢው መንደር መቼና እንዴት እንደተመሰረተች በታሪክ ተሰንዶ በብእር የተከተበ ሰነድ ባይገኝም የዋግ ሹማምንት እንደ መሰረቷት ይነገራል።
ከዋግ ሹማምንት የተወሰኑ ባላባቶች በመንደሯ ይኖሩ እንደነበርና ለስራ ባቀኑባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ የተለያዩ የዛፍና የአትክልት ዝርያዎችን ይዘው በመምጣት በቤታቸው ጓሮ ይተክሉ እና ዝርያውንም ለሃገሬው ማህበረሰብ ያስተዋውቁ እንደነበር የቀኝ አዝማች ሃይሉ ክንፉ ልጅ የሆኑት አቶ ሃብተ ማርያም ሃይሉ ይናገራሉ።
እንዲየውም ይላሉ አቶ ሃብተ ማርያም ‘’ከአባቴ የባህር ዛፍ እንጨት የሚለምን ከመጣ የባህር ዛፍ ችግኝ ወስዶ አሳድጎ እንዲመልስ ይደረግ ነበር’’ ብለዋል።
‘’ለዛም ነው በግቢው መንደር ለእፅዋት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው እና እድሜ ጠገብ ዛፎች የሚበዙት’’ ሲሉም አስረድተዋል።
የአሁኑ ትውልድም ለእፅዋት ልዩ ትኩረት በመስጠት የአካባቢውን የቀደመ ልምላሜ ይበልጥ ለማጠናከር እየተጋ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ነባሩን ደን በመንከባከብና በመጠበቅ፣ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ነባር የደን ችግኞችን በመትከልና በማልማት የአካባቢያቸውን ገጽታ የመቀየርን አደራ የተረከቡ ነዋሪዎች መገኛ ነው "ግቢው መንደር"።
ለዚህ መንደር አረንጓዴ መልበስ፣ ውብና ማራኪ መሆን ደግሞ እንደ አርሶ አደር ወንድሙ ሃይሉ ያሉ ታታሪ የመንደሯ ነዋሪዎች የስራ ትጋት በግንባር ቀደምትነት ይነሳል።
አርሶ አደር ወንድሙ ሃይሉ ስለመንደሯ ሲያብራሩ ‘’በጊቢው መንደር ፆም የሚያድር መሬት የለም‘’ በማለት ይጀምራሉ፡፡ ተራራዎቿ በባህር ዛፍ ፅድ፣ በወይራና በሌሎች ነባርና አዳዲስ ደኖች መሸፈናቸውን በማስረገጥ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
የመንደሯ ሸለቆዎችና የእርሻ መሬቷ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ጥቅል ጎመን፣ ድንች፣ ሽንኩርትና ሌሎች አትክልቶችና ፍራፍሬዎች የሚመረቱባት የበለጸገች መንደር እንደሆነችም ይገልጻሉ።
‘’በመንደሯ ያሉ እድሜ ጠገብ ዛፎች ከቀደምት አባቶቻችን የወረስናቸው የልምላሜ መገለጫዎች ከመሆናቸውም ባለፈ አባቶቻችን ለእፅዋት ያላቸውን ክብር ማረጋገጫ ናቸው።’’ በማለት ‘’የበለጠ በመጠበቅና በማልማት ከአባቶቻችን የወረስውን የአካባቢ ልምላሜ ለልጆቻችን ለማውረስ እየተጋን ነው’’ ብለዋል።
አርሶ አደሩ በመኖሪያ መንደራቸው አካባቢ ያሉ ነባር ደኖችን ከመንከባከብ ባሻገር የተራቆተውን መሬት ተንከባክበው ሶስት ሺህ የባህር ዛፍ ደን እያለሙ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በተያዘው የክረምት ወራትም ሁለት ሺህ ችግኞችን ለመትከል አቅደው ስራ መጀመራቸውን የገለፁት አርሶ አደር ወንድሙ የአካባቢያቸው ልምላሜ አሁን ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ እስኪሸጋገር የአረንጓዴ ልማት ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።
‘’ሁሉም የመንደራችን ነዋሪ ለእፅዋት ትልቅ ክብር ያለው በመሆኑ ተተኪው ትውልድም አርዓያውን እንዲከተል ትምህርት እየሰጠን እንገኛለን።’’ ብለዋል።
የአርሶ አደር ወንድሙ ሃይሉ ልጅ የሆነው ወጣት አበባው ወንድሙ በበኩሉ በመንደራቸው ያለውን ልምላሜ ለማስፋት በግልና በማህበር ተደራጅው እስከ አምስት መቶ ዛፍ ተክለው እየተንከባከቡ መሆኑን ገልጿል።
‘’የጀመርነውን ተግባር በቀጣይ አጠናክረን ለማስቀጠል በተያዘው ክረምት ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል የአባቶቻችንን ፈለግ ተከትለን አካባቢያችን በአረንጓዴ አሻራ ልማት ታዋቂ እንድትሆን እየሰራን እንገኛለን’’ ብሏል።
የመስቀሎ ቀበሌ ሊቀ መንበር አቶ ታዴ ጌታሁን በበኩላቸው ግቢው መንደር በአረንጓዴና በመስኖ ልማት ስራ ከቀበሌያቸው ሞዴል መንደር መሆኑን አመልክተዋል።
ሌሎች የቀበሌያቸው መንደሮችም ከግቢው ተሞክሮና ልምድ በመውሰድ በአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ መነቃቃት እያሳዩ ነው ያሉት አቶ ታዴ ተሞክሮውን በመውሰድ በቀበሌያቸው እፅዋትን መቁረጥና ማውደም እንደነውር የሚቆጠርበት ስርዓት ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሞገስ ሃይሌ እንዳሉት የግቢው መንደር አርሶ አደር በአረንጓዴ ልማት ከመሳተፍ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ አትክልትና ፍራፍሬ የሚመረትባት መንደሯ የሷን ተሞክሮ ወደ ደብረ ወይላ፣ ዛሮታ፣ ሲልዳና ኒሯቅ ቀበሌዎች በማስፋት ቀጠናውን የአረንጓዴ ልማት መገለጫ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025