አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቻይና የግብርና ምርታማነትን በሚያሳድጉ አዳዲስ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከቻይና ሻንጋይ ጂያኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ኢንጅነሪንግ ልኡካን ቡድን ጋር ትብብርን የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በእውቀት ሽግግር፣ ምርምር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች የትብብር ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ለዚህም የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያላትን አቅምና ምርታማነትን ለሚያሳድጉ ምርምሮች ትኩረት መስጠቷን አንስተዋል።
በምርምር ላይ የተመሰረቱ የፖሊሲ ውሳኔዎችን በመስጠት በምግብ ራስን ለመቻል ተግባራዊ በተደረጉ መርሃ-ግብሮች ለውጦች መመዝገባቸውን በመጠቆም በስንዴ ሰብል የተገኘውን ስኬት ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።
የቻይና ሻንጋይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርሲቲ የደረሰበት የምርምር ቴክኖሎጂ የግብርና ምርትን በእጥፍ የሚያሳድግ እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ምርታማነትን ለመጨመር እያከናወነ ያለውን ተግባር የበለጠ ለማሳደግና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ትብብሩን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የቻይና ሻንጋይ ጂያኦቶንግ ዩኒቨርሲቲ ልኡካን ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ጁን ሱይ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የተለያየ ስብጥር ያላቸው የሰብል አይነቶች እንዳላት በመጠቆም ጥራትና እሴትን ለመጨመር በምርምርና ቴክኖሎጂ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት የእውቀት ሽግግር መፍጠር የሚችሉባቸው ዘርፎች መኖራቸውን ገልጸው ቻይና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ካላት ስኬት ኢትዮጵያ መማር እንደምትችል ጠቁመዋል።
በምግብ ሳይንስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ ትብብሩ እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክተር አልጋነሽ ቶላ(ዶ/ር) ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የቻይና ሻንጋይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርስቲ ከ6 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ትብብር እንዳላቸው ተገልጿል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025