የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም ዘርፎች ዘላቂና አካታች የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል -የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

Jul 23, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2017(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም ዘርፎች በኢትዮጵያ ዘላቂ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የግሉን ዘርፍ ተዋናዮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የፋይናንስ ተቋማትን በማሳተፍ በዘላቂ ልማት፣ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊና በንግድ ዙሪያ የሚመክር የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግል ዘርፍ መድረክ እየተካሄደ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትብብር ባዘጋጁት በዚህ ጉባኤ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የባንክ ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ታድመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ ለአካታች ፋይናንስና ልማት የብድር አገልግሎት ማመቻቸት፣ የኢንቨስትመንት ከባቢ በኢትዮጵያ እና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ በመርሀ ግብሩ የፓናል ውይይት የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ባለፈው አንድ ዓመት ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፓለቲካዊ ዘርፎች የሚቀይር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን በኃይል፣ የፍጥነት መንገድ እና በተለያዩ የትብብር መስኮች በማስተሳሰር የቀጣናውን ትብብር ማዕከል ማድረግ መቻሏን ገልጸዋል።

የግሉን ዘርፍ ጨምሮ በሁሉም ፈጣን ዘላቂና አካታች የዕድገት ዘርፍ የተመዘገበበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ፣ የዋጋ ግሽበትን በግማሽ በመቀነስ፣ የባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን የአገልግሎት ሽፋን በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡንም አንስተዋል።

መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የበጀት ጉድለትን ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሳይወስድ ያጠናቀቀበት ዓመት መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ወደ ስምንት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ማሳደጓን በመጥቀስ፤ በሪሚታንስ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ የግሉ ዘርፍ መድረክ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተዋንያንን የሚያገናኝ መሆኑን በመግለጽ፣ ዘርፉ ለውጭ ውድድር ክፍት መደረጉን ተከትሎ በፍትሐዊነት ለመወዳደር የሚያስችል ስራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.