የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተቋማትን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት ያስችላል-በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

Jul 21, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 11/2017 (ኢዜአ):-የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እውቀትን በማስፋፋት፣የግለሰቦችንና የተቋማትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት ቁልፍ ዓላማው መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።


የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ "በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" የተገኙ ስኬቶች ላይ ተመስርቶ አዳዲስ የዲጂታል እድገቶች ላይ ያተኮረ ነው።

ስትራቴጂው አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስማርት ከተሞችን፣ ድንበር ተሻጋሪ ኢ-ኮሜርስ ፣ ዲጂታል ሉዓላዊነትን የመሳሰሉ ጽንሰ ሃሳቦችን በማካተት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ስትራቴጂው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስለሚፈጥሩ የስራ እድሎች፣ አካታች እና ፍትሃዊ ልማትን እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዓላማ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የዲጂታል እውቀትን በማስፋፋት እና የተቋም አቅምን በመገንባት የግለሰቦችን እንዲሁም የተቋማትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት የስትራቴጂው ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠን፣ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ተደራሽነትን ማሳደግ እና ኢትዮጵያን ለዲጂታል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ ማድረግ ከስትራቴጂው ዓላማዎች መካከል እንደሚካተቱ አክለዋል።

አገራዊ ዳታዎችንና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አዝማሚያዎችን እና አገራዊ የልማት ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን የዲጂታል ልማት ምሰሶዎችንና የትኩረት አቅጣጫዎችን የለየ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአይሲቲ ማህበር ፕሬዝዳንት ይልቃል አባተ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ እያከናወነች ያለውን ስራ በሰፊው ለመተግበር የሚያስችል ነው።


በተጨማሪም ዜጎች በዲጂታል ዓለም ተፎካካሪ እንዲሆኑ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አክለዋል።

ስትራቴጂው ኢትዮጵያን የዲጂታል ማዕከል ለማድረግ እንደሚያስችል የተናገሩት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ባህሩ ዘይኑ ናቸው።


የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.