ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የስርዓተ ምግብ ጉባኤው በኢትዮጵያ እና ጣልያን የጋራ አዘጋጅነት የሚካሄድ ነው።
ጉባኤው ከሚወያይባቸው አጃንዳዎች መካከል እ.አ.አ በ2021 በጣልያን የተካሄደው የመጀመሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ አጀንዳዎችና የሀገራት ቃል ኪዳኖች አፈጻጸም ይገኝበታል።
በወቅቱ ጉባኤውን የመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዓለም ስላለው የምግብ እህል አቅርቦት ችግር ምላሽ የመስጠት አስፈላጊነት፣ በመንግስታትና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ምርታማነት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ መከላከል ላይ ያተኮረ ንግግር አድርገው ነበር።
የዓለም የምግብ ስርዓት ተሰብሯል በዚህም ምክንያት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው በመሆኑም ስብራት የገጠመው የዓለም የምግብ ስርዓት ማሻሻያ ያስፈልገዋል ነበር ያሉት።
በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ባላቸው ውስን ሀብቶችና የእዳ ጫና ምክንያት በምግብ ስርዓታቸው ላይ በሚፈለገው ደረጃ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ እጅ አጥሯቸዋል ብለዋል።
ይህም ሀገራት በተለይ ለዜጎች የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እጅጉን ፈታኝ እንዳደረገባቸው በመጥቀስ።
ዋና ፀሐፊው ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ገንዘብ በዘላቂ የምግብ ስርዓቶች ላይ ፈሰስ ማድረግ፣ መንግስታትና የንግድ ተቋማት ከትርፍ ይልቅ ሰውን ያስቀደመ የምግብ ስርዓት መገንባት እንደሚገባቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ሁሉም ዜጎች ጤናማ ምግብ የሚያገኙበትን አዳዲስ መንገዶች መፍጠር በሶስተኛ ደረጃ በጉተሬዝ የተቀመጠው የመፍትሔ አማራጭ ሲሆን ሀገራት የምግብ ገበያቸውን ክፍት እንዲያደርጉ እንዲሁም የንግድ እና የኤክስፖርት ገደቦች እንዲያነሱ መጠየቃቸውም እንዲሁ።
አንቲኒዮ ጉቴሬዝ በሮሙ ጉባኤ ላይ ስድስት የቅድሚያ ትኩረት የሚያሻቸው የተግባር ምላሽ መስኮችንም ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ሀገራትም ለጉዳዮቹ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የዋና ጸሐፊው ስድስቱ የትኩረት መስኮች :-
1. የምግብ ስርዓት ስትራቴጂዎችን ከሁሉም ብሄራዊ ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር የሚያደርግ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፤
2. ሁሉን አሳታፊ አካሄድን በመከተል ሁሉንም ዘርፎችና ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት የስርዓተ ምግብ አስተዳደር መፍጠር፤
3. በጥናት፣ ዳታ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፤
4. ሁሉን አቀፍ የዕቅድ ዝግጅትና ትግበራን ማጠናከር፣ በዚህም ውስጥ ሴቶችንና ወጣቶችን ጨምሮ ዜጎችን ማካተት፤
5. በመንግስት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍ አማካኝነት የንግዱ ማህበረሰብ በምግብ ስርዓት ውስጥ ያለውን ድርሻ በማሳደግ ዘላቂ የምግብ ስርዓትን ማረጋገጥና የተጠያቂነት አሰራሮችን ማጠናከር እንዲሁም፤
6. የአጭርና የረጅም ጊዜ የአነስተኛ ወለድ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ፣ የበጀት ድጋፍና የእዳ ሽግሽግ ማድረግ ናቸው።
ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስርዓተ ምግብ ጉባኤ የተመድ ዋና ጸሐፊ የተግባር ምላሽ የሚሹት ጉዳዮች አፈጻጸም ምን ላይ ይገኛል? የሚለውን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025