የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው የልማት ሥራዎች ተሳትፏቸውን ያጠናክራሉ

Jul 10, 2025

IDOPRESS

ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 3/2017 (ኢዜአ)፡-በአካባቢያቸው በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የቴፒ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ከ30 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አገልግሎት መግባት የአካባቢውን ጸጋዎች በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዓለሙ ጣማ እንደገለጹት መንግስት በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በማልማት ለህዝብ ጥቅም ለማዋል እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።


ለዚህም የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ዓለሙ፣ ከ30 ዓመታት በኋላ ዳግም አገልግሎት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሰይድ ጦይብ በበኩላቸው ሰሞኑን በአካባቢው የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


ለምረቃ ከበቁ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ድልድይ እና የቡና ጥራት ምርምርና ሰርቲፊኬሽን ማዕከልን በማሳያነት ጠቅሰው፣ ለአካባቢው የልማት ሥራዎች የሚያደርጉትን አስተዋጾ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።


ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአካባቢያቸው በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ባህሩ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።

ለዘመናት ሲነሳ የነበረው የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄያቸው ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በሦስት አቅጣጫ ወደከተማዋ እየተገነቡ ያሉ መንገዶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያፋጥነው ተናግረዋል።


የመሠረተ ልማት መስፋፋት ሰርቶ የመለወጥ ዕድልን የሚያሰፋና ለሥራ የሚያነሳሳ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ታምራት ታከለ ሌላው የከተማው ነዋሪ ነው።

አሁን ላይ በአካባቢው ያለው የልማት እንቅስቃሴ የተሻለና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግሮ፣ ለአካባቢው ልማት መፋጠን የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።


በሸካ ዞን ግንባታቸው የተጠናቀቁ አምስት መሠረተ ልማቶች ሰሞኑን የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.