የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ መንግሥት ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች በተጨባጭ የሕብረተሰቡን ሕይወት እየቀየሩ ነው - ሳዳት ነሻ

Jul 4, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች በተጨባጭ የሕብረተሰቡን ሕይወት እየቀየሩ መሆናቸውን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሳዳት ነሻ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በምዕራብ ጉጂ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን እየጎበኘ ነው።

በጉብኝቱም የስንዴ ክላስተር፣ የቀበሌ አስተዳደር አደረጃጀት፣ የባህላዊ ፍርድ ቤት፣ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችም ተጎብኝተዋል።



ጉብኝቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሳዳት ነሻ፤ በኦሮሚያ ክልል የስንዴ፣ የማር፣ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በርካታ ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

እነኚህ ኢኒሼቲቮችም አስፈላጊ የሚባሉ ዝግጅቶች ተደርገው ወደ ስራ የገቡ መሆኑን ጠቁመው በተጨባጭ የሕብረተሰቡን ሕይወት በመቀየር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም በምዕራብ ጉጂ ዞን በክላስተር በመልማት ላይ የሚገኘው የስንዴ እና የጤፍ ምርታማነት በእጅጉ መጨመሩን ተናግረዋል።


ለዚህም መንግስት አስፈላጊ የሚባሉ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ለውጤታማነቱ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የአርሶ አደሩ ህይወት በተጨባጭ እየተቀየረ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌ አደረጃጀት የህብረተሰቡን እንግልት በተግባር ያስቀረ፤ አገልግሎት በአካባቢያቸው እንዲያገኙ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞንም የቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ተገንብተው ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።


በምዕራብ ጉጂ ዞን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነቡ የሚገኙ የውሃ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር ብልጽግና በቤተሰብ ደረጃ እየተረጋገጠ ለመሆኑ ማሣያ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.