የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የዲፕሎማሲ መመሪያ ሰነዱ የሪፎርሙን ተደራሽነት ለማስፋት ያግዛል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

Jun 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2 /2017 የኢዜአ )፦የኢትዮጵያን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ የተዘጋጀው የዲፕሎማሲ መመሪያ ሰነድ የሪፎርሙን ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚያግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በቂ ግንዛቤ የሚያገኝበት መመሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ዛሬ ይፋ የሆነው "DIPLOMATIC GUIDE FOR THE HOME-GROWN ECONOMIC REFORM AGENDA" በሚል ርዕስ የተሰናዳው መመሪያ ሰነድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት፣ ዝቅተኛ የማምረት አቅምና የፕሮጀክት አፈፃፀም እንደነበረበት አስታዉሰዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በግብርና በስንዴ ምርት እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሻሻልና ተኪ ምርቶችን በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናዋን በመቀነስ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት ተርታ መመደቧን ገልጸው፣ ቀጣይነት እንዲኖረው የኢትዮጵያን አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የዲፕሎማሲ መመሪያ ሰነድም የኢትዮጵያን እምቅ አቅሞች በማስተዋወቅ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ያስችላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቃቸው የሚገባው ቀድሞ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ የመመሪያ ሰነዱ ማሻሻያው ለውጭ ባለሀብቶች የፈጠራቸው እድሎችን በሚገባ የሚያብራራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ምቹ የኢንቨስትመንት አቅም በተዘጋጀው መመሪያ ሰነድ አማካኝነት ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይም በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስመዘገበችውን ውጤት ለማላቅ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መኖር አለበት ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ሚሲዮኖች ስለኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት በኩራት የሚናገሩበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የዲፕሎማሲ መመሪያ ሰነድም የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም በጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሪፎርም እንዲደግፉ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በቀላሉ ማጓጓዣ የሚያስችል እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ የተሳለጡ የትራንስፖርት አማራጮች እንዳሉም ጠቅሰዋል።


#Ethiopian_News_Agency


#ኢዜአ


#Ethiopia

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.