የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ስሎቪንያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራን ለማጠናከር የባለሙያና ቴክኖሎጂ ድጋፍ ታደርጋለች -የስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

Jun 6, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ስሎቪንያ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራን ለማጠናከር የባለሙያና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደምታደርግ የስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሳ ፒርክ ሙሳር (ዶ/ር) ገለጹ።

አገሪቱ በዘመናዊ ንብ ማነብ ላይ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ በማጋራት ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ትሰራለችም ብለዋል።

በዚሁ ወቅት ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን በዚህም የስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሳ ፒርክ ሙሳር (ዶ/ር) እና ልዑካቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሳ ፒርክ ሙሳር (ዶ/ር) እንዳሉት ስሎቪንያና ኢትዮጵያ መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው።

ስሎቪንያ በዘመናዊ ንብ ማነብ ልምድ ያላት አገር መሆኗንና በኢትዮጵያ ለዘርፉ የባለሙያና ቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የዛሬ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በሌሎች መስኮችም ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የንብ ማነብና ከተማ ግብርና ስራ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና አካባቢን ለመጠበቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅና የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ስራ ከአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂ ጋር የተሰናሰለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ የጋራ የልማት ግብ ካላቸው ጋር በትብብር እንደምትሰራም ገልጸዋል።

በአዲስ ዙ ፓርክ በይፋ የተጀመረው ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ የአለም አቀፍ ትብብር ማሳያ ጭምር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለትምህርትና ለቱሪዝም ዘርፍም ጠቃሚ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.