የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር ማስተሳሰሩን እያሰፋ ነው

Jun 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር የማስተሳሰር አገልግሎቱን እያሰፋ መምጣቱን የአየር መንገዱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ረታ መላኩ ገለፁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግዛት ወደ ሆነችው ሻርጃህ ከተማ ትናንት አዲስ በረራ ጀምሯል።

በበረራ ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሃማድ ፋሪድ አልባዳዊ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


በዚህ ወቅት የአየር መንገዱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ረታ መላኩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እአአ በ1946 ወደ የመን በጀመረው በረራ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያለውን ትስስር ያስጀመረ ነው።

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ከ50 አመት በፊት እአአ በ1976 ወደ አቡዳቢ በረራ ማስጀመሩንና መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመካከለኛው ምስራቅ እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር የማስተሳሰር አገልግሎቱን እያሰፋ መምጣቱን አንስተው፤ አሁን ላይ በ13 የመካከለኛው ምስራቅ መዳረሻዎች በሳምንት 120 የሰውና የካርጎ በረራ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእዚህም መካከል በዱባይና ሻርጃህ በሳምንት ከ30 በላይ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የረጅም ዘመን ታሪክ ያላትና የአለም የንግድ ማዕከል ወደ ሆነችው ሻርጃህ የተጀመረው አዲሱ በረራ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

አዲስ የተጀመረው በረራ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካን የንግድ፣ ቱሪዝምና የባህል ልውውጥ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑንም ጠቁመዋል።


የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሃማድ ፋሪድ አልባዳዊ በበኩላቸው፤ አዲሱ የበረራ አገልግሎት የሁለቱን ሀገራት የባህልና ህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን አንስተው፤ አዲስ የተጀመረው የበረራ መዳረሻ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ለንግድ አዲስ በር የሚከፍትና በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ የሚያስተሳስር መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.