የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የክልሉን የልማት ግቦች ለማሳካት የንግዱ ማህበረሰብ የላቀ ሚና መጠናክር አለበት- ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

May 30, 2025

IDOPRESS

ሠመራ፤ ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የተቀየሱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ የላቀ ሚናውን እንዲያጠናክር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አሳሰቡ።

"ለሁለንተናዊ ብልፅግና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ከወረዳ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የማጠቃለያ መድረክ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።


የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልል ደረጃ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ዕውን ለማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ ሚና የላቀ ነው።

ለተግባራዊነቱም የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በወቅቱ የመክፈል ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው፣ የንግድ ስርአቱን በማዘመን ሂደት ከአሰራር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊነትን ተላብሶ የግብይት ስርአቱን ማሳለጥ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር ናቸው።


ቢሮው ለንግድ ሥርአቱ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑንም አመልክተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ አቶ አወል አብዱ በበኩላቸው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄዎች ለመመለስ እስከ ታች ድረስ በመውረድ እየተሰራ ነው ብለዋል።


ነጋዴው ገቢውን በማሳወቅና ግብሩን በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዘነበች አብርሃ በበኩላቸው "መንግስት የሚገባውን ገቢ በትክክል እንዲያገኝ በከተማ አስተዳደሩ ፈጣንና አስተማማኝ የግብር አሰባሰብ ስርአት ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል።

በነጋዴው ማህበረሰብ የሚነሱና ከግብር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ አግኝተው ነጋዴው ለሀገር እድገት የሚያበረክተውን ድርሻ ማጉላት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የአፋር ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቦርድ አባል አቶ ከበደ መሐመድ በበኩላቸው፣ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና የመንግስት ገቢ ባግባቡ ለመሰብሰብ የንግዱን ማህበረሰብ ማወያየት ወሳኝ መሆኑን ጠቅስዋል።

ከዚህ ባለፈ የንግድ ሥርአቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች መሻሻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.