የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የኢትዮጵያ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነት የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

May 30, 2025

IDOPRESS

አዳማ፤ ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነት የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ከዓለም አቀፍ የነፍሳት ሥነ-ምህዳር እና ሥነ-ህይወት ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር በማር ምርት ላይ በማተኮር ባዘጋጀው ረቂቅ ደረጃዎችና ሰርተፊኬሽን ስኪሞች ከክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከርና ለማስተዋወቅ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።


በመድረኩ ማጠቃለያ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ(ዶ/ር) እንዳሉት ተቋሙ የምርቶችንና አገልግሎቶችን ጥራት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም መንግሥት የማር ምርትን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ ይህም በልማቱ የኢትዮጵያን ብራንድ መገንባት ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፈረመችው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነት መሰረት ለገበያ ከሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ውስጥ የማር ምርት አንደኛው በመሆኑ የጥራት ደረጃ ሊያሟላ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የማር ምርት ጥራትና ደረጃ ለማውጣት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ይህም የንግድ አድማሱን ለማስፋፋት እንዲሁም የተስማሚነት እና የደረጃ ጉዳይም ተፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ ጎልቶ እንዲወጣ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።


በኢንስቲትዩቱ የደረጃዎች ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ይልማ መንግሥቱ በበኩላቸው ሀገራችን በማር ምርት ካላት አቅምና የተፈጥሮ ጸጋ አንጻር ከዘርፉ ጥቅም አላገኘችም ብለዋል።

ይህንን ለማሻሻል ተቋሙ የማር ጥራትና ደረጃዎችን በማውጣት በሚመለከተው አካል ለማጸደቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የወጣው ደረጃም ከዓለም አቀፍ መስፈርትና ደረጃ ጋር መጣጣሙን አረጋግጠዋል።

ይህም የሀገራችንን የማር ምርት ዓይነት፣ ባህሪና አጠቃላይ ምርቱን የማስተዋወቅ ስራዎችን ለመስራትና ከዓለም አቀፉ መስፈርትና ደረጃ ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት መጎልበት እንደሚረዳ አውስተዋል።


በዓለም አቀፍ የነፍሳት ሥነ-ምህዳር እና ሥነ-ህይወት ምርምር ማዕከል የገበያ ልማት ሥርዓት አስተባባሪ ሄኖክ መቻል፤ ማዕከሉ በግብርና ልማት ፕሮግራም ብቻ በሀገሪቱ አንድ ሺህ ወጣቶችን በማር ሀብት ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ሂደት የማር ደረጃ መስፈርቶችን በማውጣት ሂደት ለኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።


ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ንብ ልማት ማሕበር የቦርድ ሰብሳቢ አሰፋ አማልደኝ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ ባለሀብቶችንና አነስተኛ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ሁለት ሚሊዮን ንብ አንቢዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

እነዚህ አካላት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት ካልቻሉ በህብረተሰብ ጤናና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል ስላልሆነ ለምርቱ የጥራትና መስፈርት ደረጃ መውጣቱ ልማቱን ለማስፋፋትና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.