አዲስ አበባ፤ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ኢንሹራንስን የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ ማድረግ አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
51ኛውን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፈረንስና ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ኮንፈረንሱ ''የክፍያ ሚዛንን ማስተካከል፦ የአፍሪካ የእዳ ጫና፣ የሃገራት እዳ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራል? በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ በርካታ ሀገራት በዕዳ ጫና መጨመርና በበጀት ሚዛን መዛነፍ ፈተና ላይ መውደቃቸውን አንስተዋል።
ይህም ለኢንሹራንስ ድርጅቶች ዋነኛ ስጋት መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኢንቨስትመንት ምህዳር፣ ከንብረት ደህንነት፣ ከደንበኛ ፍላጎት እስከ ኢኮኖሚ መረጋጋት ያላቸው ሚና ላይ ከባድ ፈተና እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በመሆኑም የፈተና መቀልበሻ ዘዴዎችን የመፈተሽና በጋራ የወደፊት እጣ ፈንታን መቀየስ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ኢንሹራንስ አሁን ካለበት አውድ መሻሻልና መጠናከር አለበት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ መሆን እንደሚገባው በማንሳት የእያንዳንዱ ቤተሰብ ዋስትና፣ የብድር አንቀሳቃሽ እና የኢንቨስትመንት ስበት ቁልፍ መሳሪያ እንዲሆን መስራት የግድ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ፈተናዎችን የሚቋቋምና ዘመናዊ ኢኮኖሚ እየገነባች፣ ተወዳዳሪነትን እያሳደገች፣ የግሉን ዘርፍ እያሳተፈች መሆኗንም ገልጸዋል።
ፈጠራን የሚያበረታታ፣ ንግድን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚስብ ዘላቂና አስተማማኝ ምህዳር እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
ለዚህ መሳካት የጠንካራ የፋይናንስ ስርዓት መኖር ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢንሹራንስ ዘርፉ ደግሞ የፋይናንስ ስርዓቱ መሠረት ነው ብለዋል።
ይህን በመገንዘብም መንግሥት ወሳኝ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጠንካራና ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ተቋም መቋቋሙን አንስተዋል።
ይህ አዲስ ተቋም ፈጠራን የሚያበረታታ፣ ውጤታማ ቁጥጥርን የሚያጠናክር እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖሊሲ ባለቤቶችን ከስጋት ይከላከላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አዳዲስ በሮችም እየከፈተች መሆኗን ጠቅሰው፥ በቅርቡ መንግሥት የማይንቀሳቀስ ንብረት አጠቃቀምና ባለቤትነትን የሚደነግግ አዲስ ረቂቅ አዋጅን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም በመኖሪያ ቤት፣ በመሠረተ ልማት እና በሪል እስቴት ለአዳዲስ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ መፍትሄዎች ትልቅ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ አመልክተዋል።
በመሆኑም ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ ገበያ መዳረሻ ለመሆን መዘጋጀቷን ጠቅሰው፥ ለዚህ ጉዞ መሳካትም መንግሥት በሙሉ አቅም እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት የአህጉሪቱ የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያድግ እያደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚህ ወቅት በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የግሉን ዘርፍ በሚያበረታታ እና ኢንቨስትመንትን በሚያረጋግጥ መልኩ በልዩ አመራር እየተተገበረ መሆኑን ተናግርዋል።
ብድርን በተመለከተ ያሉ ችግሮች ሲፈቱ የኢንሹራንስ ዘርፉን በሚፈለገው አቅም ማሳደግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በፋይናንስ ዘርፉ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያረጋግጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ ነው ብለዋል።
በፋይናንስ ዘርፉም ህግ ከማሻሻል ጀምሮ በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ የአሠራር ሪፎርሞች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፋይናንስ ዘርፉ የተሰሩ አጠቃላይ ስራዎች የኢንሹራንስ ዘርፉን ዕድገትን በማገዝ በኩል ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የዲጂታል ሽግግር በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ለማምጣት እና የኢንሹራንስ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ አበርክቶ እንዳለውም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025