አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ የአይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጉባኤ የኢትዮጵያን በተለይም የአዲስ አበባን ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገት እንድንጎበኝ ምቹ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ የአይዲ ፎር አፍሪካ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
ተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገትና በህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት መደመማቸውንም ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ትላልቅ አለም አቀፍና አህጉራዊ ሁነቶችን በስፋት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።
በሁነቶቹ ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ እንግዶች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ባሉ ፈጣንና ትላልቅ የልማት ተግባራት መደነቃቸውን ይገልጻሉ።
ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው የአይዲ ፎር አፍሪካ አለም አቀፍ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ከጋምቢያ፣ ከሴኔጋልና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ከተማ የመጡ ተሳታፊዎች ስለ አዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ዕድገት በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከጋምቢያ የመጡት ኮዶ ሱሶ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት የመሄድ አጋጣሚ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አዲስ አበባን ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ለመሸጋገር ከሚኖራቸው ጥቂት ቆይታ ውጪ ሙሉ ከተማዋን የመጎብኘት ዕድል እንዳልገጠማቸው ተናግረዋል።
በአይዲ ፎር አፍሪካ ጉባኤ ለመሳተፍ ከሳምንት በላይ በአዲስ አበባ ቆይታ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያን በተለይም አዲስ አበባን በአግባቡ ለመጎብኘት ምቹ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት።
በቆይታቸውም በከተማዋ የመሰረተ ልማት ዕድገትና በህዝቡ እንግዳ አቀባበል እጅግ መደሰታቸውን ነው የገለጹት።
ከሴኔጋል የመጡት ሌላው የጉባኤው ተሳታፊ ኮምባ ሴኔ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የመምጣት ዕድሉ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት ከምንግዜውም በላይ ፈጣንና አስደማሚ እንደሆነባቸው ገልጸው፤ የህዝቡ ተግባቢነትና እንግዳ ተቀባይነትም ልዩ መሆኑን አንስተዋል።
ከዱባይ የመጡት ጀርመናዊው ዛቪየር ሮስት በበኩላቸው ከተማዋ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥን መሰረተ ልማት እንዳላት ተናግረዋል።
በዚህም በቀጣይ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ የመምጣት ፍላጎታቸው እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰው፤ ሌሎችም ከተማዋን የመጎብኘት ዕድል እንዲኖራቸው ተመኝተዋል።
የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርአያስላሴ በበኩላቸው ከጉባኤው ጎን ለጎን እንግዶቹ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም ደስተኛ መሆናቸውንና የኢትዮጵያ ቆይታቸውም የማይረሳ መሆኑን መግለጻቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025