የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ክልሎች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ ነው

May 26, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፦ክልሎች የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ አስታወቁ።


የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓት በ169 የፌዴራል ተቋማትና በ93 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቻቸው ተግባራዊ ተደርጓል።


በአገር አቀፍ ደረጃ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ክልሎችም ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አመልክተው፤ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሥርዓቱ ገብቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።


ኦሮሚያ ክልል ዝግጅቱን ጨርሶ ሥልጠና በመስጠት ሂደት ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሶማሌ ክልል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ለ2018 ዓ.ም የግዥ ሥርዓታቸውን በኤሌክትሮኒክ ለመፈጸም የዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል።


በበጀት አመቱ ሁሉም የፌደራል ተቋማት የግዥ እቅዶቻቸውን በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት ማቀዳቸውን ተናግረው፤ ይህም ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።


በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት 533 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው ግዥዎች በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት መፈጸማቸውን ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል።


ስርዓቱ ለግዥ የሚወጣውን ወጪና ጊዜ ከመቆጠብ እንዲሁም የሰነዶች ማጭበርበርን ከማስቀረት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ማስገኘቱን ተናግረዋል።


በስርዓቱ አተገባበር ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚረዳ የኢ-ለርኒንግ ሲስተም ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።


የመንግስት ግዥ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማረ ይገዙ በበኩላችው፥የንብረት ማስወገድ ስራ ተቋማት በሚያቀርቡት የይወገድልኝ ጥያቄ ላይ መመስረቱ ውጤታማ አለመሆኑ ተለይቷል ብለዋል።


በዚህም በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የሚወገዱ ንብረቶች ያላቸውን የተመረጡ ተቋማትን በመጎብኘትና ንቅናቄ በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።


በበጀት አመቱ አስር ወራት የተከናወነው የንብረት ማስወገድ ስራ አፈጻጸም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ56 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ነው የጠቀሱት።


ይህም የመንግስትን ንብረት ከብክነት ከማዳንና ገቢ ከመጨመር አኳያ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።


ባለፉት አስር ወራት በማዕቀፍ ስምምነት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የጋራ መገልገያዎች እና 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግዢ መፈጸሙንም ገልጸዋል።


ዕቃዎቹ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ማለፋቸውን ገልጸው፥ይህም ፍትሃዊ፣ተወዳዳሪና ግልጽ አሰራር መፍጠር ከመቻሉ ባለፈ ህገ ወጥነትን ማስቀረቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.