የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሒሳብና ሳይንስ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ተማሪዎች የማብቃት ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ነው - ትምህርት ሚኒስቴር

May 26, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ ግንቦት 15/2017(ኢዜአ)፦ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሒሳብና ሳይንስ ልዩ ተሰጥዖና ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች የመለየትና የማብቃት ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የሒሳብ ትምህርት ልህቀት ማዕከል ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ 2ኛው ሀገር አቀፍ የሒሳብ ትምህርት ኦሎምፒያድ የተካሄደ ሲሆን በዘርፉ ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሚወክሉ ተማሪዎችም ተመርጠዋል።


በትምህርት ሚኒስቴር የሒሳብ፣ የሳይንስና ስነ-ጥብብ ማበልጸጊያ ዴስክ ተወካይ ተስፋ ተዘራ እንዳሉት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሒሳብና ሳይንስ ልዩ ተሰጥዖና ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች የመለየትና የማብቃት ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ነው።

የሒሳብ ጽንሰ ሃሳብን በመረዳት ከታዳጊዎች ጋር እንዲዋሃድ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

ለዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሒሳብና የሳይንስ ማበልጸጊያ ተቋማትን በመጠቀም በዘርፉ ልዩ ተሰጥዖና ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች የመለየትና የማብቃት ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተለይ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የፈጠራ ስራዎችን በማውጣትና በማወዳደር የላቁትን ማበልጸግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሒሳብ ልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ኦሎምፒያዱም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።


የሒሳብ ትምህርት በቴክኖሎጂና በማህበረሰብ የኑሮ ለውጥ ላይ ጉልህ ሚና አለው ያሉት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሀብታሙ ተመስገን(ዶ/ር) ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው በተግባር ሳይንስ የትኩረት ዘርፍ ላይ መመደቡን ተከትሎ የተግባርና የፈጠራ ስራዎችን በምርምርና በጥናት ለማዳበር እየጣረ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በሒሳብና በሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ብቁ ታዳጊዎችን ለማፍራት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ኦሎምፒያዱ በዩኒቨርሲቲው መካሄዱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ የኢንጂነሪንግና የሒሳብ ትምህርቶች ተግባር ተኮር ስልጠና ማዕከል(ስቲም ፓወር) ዳይሬክተር ስሜነው ቀስቅስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው በኢትዮጵያ ከ65 በላይ ቤተ ሙከራዎችን በማደራጀት ለቅድመ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርትና ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የታዳጊዎችን የፈጠራ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የኢ-ኮሜርስ፣ የሶፍት ዌር ግንባታና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ እያደረገች ያለውን ጥረትና ተሳትፎ የሚያጠናከር ነው ብለዋል።


የኢትዮጵያ የሒሳብ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሳሙኤል አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው በ2ኛው ኦሎምፒያድ ከመላ ሀገሪቱ ከ6ሺህ 100 በላይ ተማሪዎች በውድድሩ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ሶስት የውድድር ምዕራፎች በማለፍም በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሰባት ተማሪዎች ዛሬ መለየታቸውን ነው ያስረዱት።


በውድድሩ 1ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኪዳነ ምህረት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዘርዓ ገብረፃድቅ ሒሳብ ከቁጥር ስሌት ባሻገር የማሰብና የፈጠራ ክህሎትን የሚያዳብር ነው ብሏል።

በቀጣይም ጠንክሮ በመስራት በምስራቅ አፍሪካ የሀገሩን ስም ከማስጠራት ባሻገር የፈጠራ ስራዎችን በማከናወን የሒሳብ ትምህርትን የሕይወቱ አካል ለማድረግ እንደሚጥርም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.