ባሕርዳር/ ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፡- የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማቅረብ ገበያን ከማረጋጋት ባሻገር በአካባቢያቸው ሰላምን ለማፅናት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በአማራ ክልል የንግድ ማሕበረሰብ አባላት አስታወቁ።
"ለሁለተናዊ ብልጽግና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና " በሚል መሪ ሀሳብ በባሕርዳር እና ደብረብርሃን ከተሞች ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።
በባሕርዳሩ ውይይት ተሳታፊ የንግዱ ማሕበረሰብ አባላት በሰጡት አስተያየት ህገ ወጥ ንግድን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ በንቃት በመሳተፍ ለሰላም መከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ቀለም ወርቅ መላኩ እንዳሉት፤ ችግሮችን በመቋቋም ሰርተው ካገኙት የመንግስትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ለህጋዊ ነጋዴው ትልቅ እንቅፋት እየሆነ ያለውን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በትብብር መግታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህም ከመንግስት ጎን በመሰለፍ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ የእህል ነጋዴ አቶ አለሙ ሙሉነህ በበኩላቸው፤ በነበረው ችግር ምክንያት የንግዱ ማህበረሰብ ላይ ጫና ፈጥሮበት መቆየቱን አውስተዋል።
መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ሰላም መስፈኑን ገልጸው፤ ገበያን በማረጋጋት ሰላምን ለማፅናት ድጋፋቸውን በማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ እንደገለጹት፤ በህግ ማስከበር ስራ የተከናወኑ ተግባራት አሁን ላለንበት ሰላም አብቅቶናል ብለዋል።
በቀጣይ የተገኘውን ሰላም አፅንቶ ለመዝለቅ የንግዱ ማህበረሰብ ሚናውን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
ዛሬ የተካሄደው የውይይት መድረክም የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለይቶ በመፍታት የንግዱን ማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።
በተመሳሳይ በደብረብርሃን ከተማ በውይይት ከተሳተፉት መካከል አቶ ክንዴ ምንሽር እንደገለጹት፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በከተማዋ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ተመራጭ እየሆነች መጥታለች።
የተገኘው ለውጥ እንዲጠናከር ምርትን በጥራትና በብዛት በማቅረብ ገበያ ከማረጋገት ባሻገር ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለሰላም መስፈን ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ የሸዋልኡል ጌታቸው ፤ በቅንነትና በታማኝነት ግብርን በመክፈል የከተማዋ እድገት እንዲፋጠን የበኩላቸውን መወጣታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ከሌላው የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር አላሰራ ያሉ ችግሮች ተፈተው ነጻ የምርት ዝውውር ከከተማ ወደ ገጠር-ከገጠር ወደ ከተማ እንዲኖር ለማስቻልም ቅድሚያ ለሰላም መከበር ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ይርጋለም ምስጋናው ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በከተማዋ ለተመዘገቡ ለውጦች የንግዱ ማህበረሰብ ሚና የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።
የንግዱ ማሕበረሰብ በህግ ማስከበር ስራ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል የነቃ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025