የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂና ፈጣን የዕድገት ጉዞ አስገብቷል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

May 16, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂና ፈጣን የዕድገት ጉዞ ማስገባቱን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ዛሬ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በተጀመረበት መርሃ ግብር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ባንክ ኢንዱስትሪ ጅማሮ ከአንድ ምዕተ ዓመት ያለፈ ዕድሜ ቢያስቆጥርም፥ የፋይናንሱ ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የዕድሜውን ያህል ጠንካራ ቁመና ሳይፈጥር መቆየቱን አውስተዋል።

ለዚህም ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት መንግሥታት የተከተሏቸው መንግሥት መራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተፅዕኖ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ባለፉት ስርዓቶች የፋይናንስ ዘርፉ በዋናነት የመንግሥትን ብሔራዊ ጉዳዮች ለመፈጸም እንጂ፥ የግሉን ዘፍር አጣዳፊ የፋይናንስ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ አልነበረም ብለዋል።


በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ችግር ማስከተሉን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ መንግሥት ኢንቨስትመንቶችን ለማከናወን በትላልቅ ብድሮች ላይ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎት እንደነበር ጠቁመዋል።

ይህም ሀገርን በእዳ ጫና እንድትጎብጥ እና የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ ምህዳር እንዳይኖረው ማድረጉን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግሥት ዘርፈ ብዙና ስር የሰደዱ የፋይናንስ ስርዓቱን ችግሮች በጥልቀት በመገምገም ወሳኝ የኢኮኖሚ ሪፎርምና የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።

የዋጋ ግሽበትን የሚያረጋጉ፣ የዕዳ ጫናን የሚቀንሱ፣ የባንኮችን የተበላሸ የብድር ፖርትፎሊዮ የሚያስተካክሉ እና ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን የሚያቃልሉ ውሳኔዎች ማሳለፉን አውስተዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው የፋይናንስ ስርዓቱን መዛነፍ ከማስተካከል ባለፈ ተወዳዳሪና በግሉ ዘርፍ የሚመራ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማረጋገጥ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም መንግሥት በቅርቡ መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያን ወደ ሁሉን አቀፍ ዘላቂ የዕድገት ምህዋር ያስገባ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መተግበር መጀመሩን አስረድተዋል።

ሪፎርሙ በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ ተመስርቶ እየተተገበረ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በግልፅ እቅድ፣ በጠንካራ ቅንጅት እና በትክክለኛ የግብ ቅደም ተከተል እየተመራ ነው ብለዋል።


በሪፎርሙ የትግበራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቋቋም ደግሞ በመንግሥት ተቋማትና በብሔራዊ ባንክ ቅንጅት ጠንካራ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሪፎርሙ መሰረትም ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በታሪክ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም ለፋይናንስ ተቋማት በወሳኝ ጊዜ የደረሰ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመጀመሪያ የትግበራ ምዕራፍ የገቢና የበጀት ዕድገትን ጨምሮ አስደናቂ ስኬት እየተመዘገቡበት እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህም የሪፎርሙን አዋጭነትና የሚጨበጥ ግብ እንዳለው ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአጭር የትግበራ ጊዜ የተመዘገቡ ስኬቶች ለተሟላ ድል መትጋት እንዳለብን የሚያስገነዝቡ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ለዚህም የፋይናንስ ዘርፉ የተፈጠረውን ምቹ ምህዳር በመጠቀም በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ልክ መፍጠንና አድማሱን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ተደራሽነትን ማሳደግና አገልግሎትን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም በዲጂታል ሽግግር ውስጥ መሪ ተዋናይ መሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ዘርፉ ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ አካታችነትን ማጠናከርና የሰው ሀብት ልማት ላይ ማተኮር የግድ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ፈጣን ጉዞ ውስጥ ለፋይናንስ ዘርፉ ሶስት መልካም አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን ጠቅሰው፤ እነሱም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ የዲጂታል ምህዳር በፍጥነት መስፋፋት እና ያልተነካ የገበያ ዕድል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፋይናንስ ተቋማት በወሳኝ ጊዜ የተፈጠሩ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ዘርፉን ወደ ከፍታ ለማስፈንጠር ግልፅ ራዕይና ትጋት ወሳኝ እንደሆኑ አውቀው ሊሰሩ እንደሚገባም በአፅንኦት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.