መቱ፤ ግንቦት 7/2017 (ኢዜአ)፡-በኢሉአባቦር ዞን የማር ምርት የገበያ ትስስርን በማጠናከር በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መስጠቱን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ገለጹ።
''ያሉንን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ተጠቃሚነታችንንና እድገታችንን እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ የማር ምርት ኤግዚቢሽን እና ባዛር በመቱ ከተማ ተከፍቷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዞኑ ከለውጡ በፊት የማር ምርት በአብዛኛው በባሕላዊ ዘዴ ላይ የተመሰረተ ነበር።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዘመናዊ ቀፎ አቅርቦት እንዲሁም የነበረውን የሙያ እና የክህሎት ክፍተት አሟልቶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በዞኑ 330 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የማር ምርት ማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የዞኑን ማር የማምረት አቅም አሟጦ ወደ ስራ በማስገባት ለዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው ከዘርፉ የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም በዞኑ የሚገኙ ማር አምራች አርሶ አደሮች ጠንካራ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በክልሉ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ትላልቅ የግብርና ልማት ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ መሆኑን አስታውሰዋል።
የማር ምርት ኢኒሼቲቭ በክልሉ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ዜጎች ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው የማር ምርት መጠንና ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሁሉንም አቅም በማቀናጀት ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ ናቸው።
በዚህም በተለይ በግብርናው ዘርፍ ተቀርጸው በከተማና በገጠር እየተተገበሩ በሚገኙ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
''እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችም መስራት የምንችል መሆኑንና አሁንም ብዙ መስራት የሚጠበቅብን መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው'' ብለዋል።
በቀጣይ የማር ምርት መጠንና ጥራትን ለመጨመር የኤክስቴንሽንና ሙያ ድጋፍ፣ የቀፎና ተያያዥ ግብዓቶች አቅርቦት እና የገበያ ትስስር ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከሁሉም ማር አምራች የኢሉአባቦር ዞን ወረዳዎች የመጡና በማር፣ በንብ ማነብና ምርት የተሰማሩ ግለሰቦችና ማህበራትን ጨምሮ የማር ነጋዴዎችና ሸማቾች ተሳትፈዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025