የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም መደገፉን ይቀጥላል- ሼሪን ቫርኪይ (ዶ/ር)

May 15, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የባንኩ የኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኤርትራ የሰው ሀብት ልማት ፕሮግራም መሪ ሼሪን ቫርኪይ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሼሪን ቫርኪይ (ዶ/ር) ባንኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተጀመረውን የሪፎርም ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሪፎርሙ ለኢትዮጵያ ቀጣይ እድገት እና ምርታማነት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አመልክተዋል።

መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ምቹ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደነቁ ሲሆን ከኢኮኖሚው ውጪ በተለያዩ መስኮች የተደረጉ ማሻሻያዎችም መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት እያሳዩ ያሉ ዘርፎች እንዳሉ የገለጹት የፕሮግራም መሪው ዘርፎቹ የተሻለ ጥራት ያለው እድገት በማምጣት የኢኮኖሚ ሽግግሩን የመደገፍ ቁልፍ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ዘመን በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማዕቀፍ ሁሉን አቀፍ ሪፎርሞችን አድርጋለች።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎም የገቢ መጠን እና የወጪ ንግድ እድገት ያሳየ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ክምችቱም ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል። የዋጋ ንረቱም እየቀነሰ ይገኛል።

የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ሎጅስቲክስ፣ ኢነርጂ፣ ባንክና ሌሎችም ለውጭ ባለሀብቶች ቁልፍ የሆኑ ዘርፎች የባለሀብቶችን ቀልብ የሳቡ ናቸው።

የሪፎርም ኢኒሼቲቮቹን ያደነቁት ሼሪን ቫርኪይ (ዶ/ር) የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት እና ንግድ ያለውን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ሪፎርሞችን በዘላቂነት ማከናወን እንደሚገባም አመልክተዋል።

በዚህ ረገድም የዓለም ባንክ ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመሆን የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያድግ እና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አካል እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በልማት ፕሮግራም ላይ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ያላቸው ፕሮግራም መሪው በሰው ሀብት ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.