የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በመዲናዋ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል የሚቀይርና መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል የ500 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስራ ላይ ሊውል ነው

May 15, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል የሚቀይርና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል የ500 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ስራ ላይ ሊውል መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የነዋሪነትና ሲቪል ምዝገባ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ፣ የደረቅ ቆሻሻና የመንገድ ዳር ኤሌክትሪክ አገልግሎቶች በመዲናዋ ስራ አስኪያጅ መስሪያ ቤት ስር የሚተዳደሩ ተቋማት ናቸው።

ተቋማቱ በትብብርና በቅንጅት መስራታቸው የለውጥ ስራዎቹ ውጤት እንዲመዘገብባቸው ማድረጉም ተገልጿል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ለኢዜአ እንደገለፁት በመዲናዋ 500 ሚሊዮን ዶላር በሚፈጅ ኢንቨስትመንት ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኃይል መቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ይደረጋል።

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው ስምምነት የተፈፀመው ከቻይናዎቹ ሻንዥን ኢነርጂ ግሩፕ፣ ከቻይና ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ኢንጅነሪንግ እና ከጀርመኑ ኮቬናንት ኢንጅነሪንግ ድርጅት ጋር ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት እንደሚፈጅ ጠቅሰዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚውለው ወጪ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚሸፈን ሲሆን ከተማ አስተዳደሩም ለዚሁ የሚሆን መሬት እንደሚያቀርብ አስረድተዋል።

በመዲናዋ ደረቅ ቆሻሻን የመሰብሰብ አቅም 96 በመቶ ደርሷል ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ ቆሻሻን ከማስወገድ ባሻገር ወደ ሃብት የመለወጥ ስራም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ዓመታት በመዲናዋ የተካሄዱ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በመዲናዋ ባሉ 119 ወረዳዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በመደረጋቸው ለውጥ እንደተመዘገበም አብራርተዋል።

አዲስ አበባን ስማርቲ ሲቲ ማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸው በተቋማቱ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል ።

በመዲናዋ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የሲቪልና ነዋሪነት ምዝገባ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ቢሮው ባለፉት 10 ወራት የ870ሺህ ዜጎችን መረጃ/ባዮሜትሪክ ዳታን/ መውሰድ መቻሉን ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ በተደረገው የፋይዳ ምዝገባ በአዲስ አበባ ብቻ እስካሁን ከ5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.