አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን አቅም ለማሳደግ በአምስት ዐበይት መስኮች በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) በቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ሚኒስትር ሳዎ ሹሚን ከተመራ ልዑክ ጋር በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ እና ቻይና በሚዲያና ኮሙኒኬሽን የይዘት ሥራዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ማሳደግ፣ በተሞክሮ ልውውጥ እና በአቅም ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ ውይይቱ በቻይና አፍሪካ የልማት ትብብር ፎረም በተቀመጡ አስር የስምምነት ነጥቦች መነሻነት የኢትዮ-ቻይናን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በትብብር የሚሰሩባቸውን አምስት ዐበይት ጉዳዮችን በመለየት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የይዘት ሥራዎች አንዱ የስምምነቱ ዐቢይ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የሀገራቱን እውነታና ትክክለኛ ታሪክ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለሌሎች ሀገራት በተሻለ ጥራትና ይዘት ለማድረስ በጋራ ይሰራሉ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የቴሌቭዥን፣ የሬዲዮና የዲጂታል ሚዲያው አዳዲስ ለውጦችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የኢትዮጵያን ሚዲያ በቴክኖሎጂ ለማዘመን መግባባት መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በአቅም ግንባታ ዘርፍ በሰው ኃይል ልማትና ይዘት ፈጠራ ጠንካራ ሚዲያ መፍጠር የሚያስችል የድጋፍ ውይይት በማድረግ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል ነው ያሉት።
ቻይና በዲጂታልም ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ በርካታ ልምዶች የሚቀሰምባት መሆኑን ጠቁመው፤ ሁለቱም ሀገራት የተሻለ የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በቀጣይ ዝርዝር ተግባራትና የቴክኒክ ጉዳዮችን በመለየት ወደ ሥራ ለመግባት ሀገራቱ አብረው የሚሰሩበት የጋራ አቅጣጫ መቀመጡንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025