አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካና እስያ መካከል ትክክለኛ ትርክትን ለመገንባት የሚዲያ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለፁ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻይናን ማየት በሚል የተካሄደው የቻይና እና ኢትዮጵያን የሚዲያ ትብብር መድረክ ቻይና ሀወር የተሰኘ በኢትዮጵያ ሚዲያ የሚተላለፍ ፕሮግራም ይፋ የተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ራዕይ በቻይና የተሰኘ የሚኒ ድራማ ኢኒሼቲቭም ተዋውቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር)፣ የቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ሚኒስትር ሳዎ ሹሚን፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለድርሻዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) እንዳሉት መድረኩ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ወዳጅነት፣ በጋራ የመልማት ፍላጎትና የሚዲያ አጋርነታቸውን ለማጠናከር የሚረዳ ነው።
መድረኩ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ለ55 አመታት የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አብሮነት የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
የቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀው መድረክ የሀገራቱን ሚዲያ አጋርነት የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሚዲያ የሚታየው የቻይና ሀወር የተሰኘው ፕሮግራም የሁለቱን ሀገራት ሚዲያ ኢንዱስትሪና የህብረተሰቡን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል።
ያለንበት ዘመን የትስስር ቢሆንም በሀሰተኛ መረጃ የሚፈተን በመሆኑ ይህን መሰል ትስስር ትክክለኛ ትርክት ለማስረፅና የአፍሪካ እስያን አተያይ ለማጉላት እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት በመንገድና በባቡር መስመር ዝርጋታ የሚሰሯቸውን ስራዎች በትርክትና ትስስር በማጠናከር በኩል ሊያጠናክሩት እንደሚገባም አብራርተዋል።
የቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ሚኒስትር ሳዎ ሹሚን የቻይና ሀወር ፕሮግራም የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና የባህል ልውውጥን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ድራማ፣ ዶክመንተሪና የተለያዩ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ እንደሚታዩ ገልፀው፤ በቀጣይ የተሰጥዖ ማበልፀጊያ፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ትብብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው መድረኩ ሁለቱ ሀገራት 55ኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሚያከብሩበት ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰው፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርና መሰል ትስስሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄይሉ ዑመር(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከቻይና ዩኒቨርሲቲና ኢንስቲትዩቶች ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱንና ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025