ሀዋሳ፤ግንቦት 4/2017 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ያለውን የውሀ ሃብት በአግባቡ ለይቶ ለሚያስፈልገው ጥቅም ለማዋልና ለማስተዳደር እንዲቻል የተፋሰስ መረጃ ክትትል ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ረቂቅ የተፋሰስ መረጃ ክትትል ስትራቴጂክ ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀዋሳ እየመከረ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ እንዳሉት፥ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ያለንን የውሃ ሃብት በአግባቡ ለማስተዳደርና ለመጠቀም እንዲቻል የሚያግዝ ነው።
ስትራቴጂክ ዕቅዱ ምን ያህል መጠንና ጥራት ያለው የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ እንደሚገኝ፤ ለምን አገልግሎት ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል በመለየት በአግባቡ ማስተዳደር ያስችላል ብለዋል።
የህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ያለን የውሃ መጠን እንዳይቀንስ የውሀ አስተዳደራችንን ማሻሻል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሞቱማ፥ የውሀ አጠቃቀምና አስተዳደራችንን ለማሻሻል የተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
በሚኒስቴሩ የተቀናጀ ውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በበኩላቸው፥ የውሃ ሃብቱ ዘላቂ እንዲሆን የተፋሰስ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወናቸው የሚበረታታ ነው።
የተቀናጀ የውሃ ሃብት ልማት አስተዳደር በመዘርጋት ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የተፋሰስ መረጃ ክትትል ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዝግጅት አስተባባሪ አለልኝ ዘሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከ122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የገጸና ከርሰ ምድር ውሃ ሃብት እንዳለ አመልክተዋል።
በትክክል ምን ያህል የውሃ ሃብት እንዳለ ለይቶ ለመረዳት የስትራቴጂክ ዕቅዱ ፋይዳው የላቀ መሆኑን አመልክተው፥ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ኢትዮጵያ ያላትን ሃብትና ሽፋን፣የውሃ ጥራት፣ተጠቃሚዎቹና ውሃው ካለበት ወደ ሌለበት ለመውሰድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የተሟላ መረጃ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ ላይም ከሁሉም ክልሎች የውሀ፣ ኢነርጂና ማዕድን ቢሮ ተወካዮች፣የውሃ ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025