የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመጠናከራቸው በወቅቶች ሳንገደብ በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል - አርሶ አደሮች

May 13, 2025

IDOPRESS

ሆሳዕና፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመጠናከራቸው በወቅቶች ሳንገደብ በመስራትና በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል ሲሉ የሀዲያና የምስራቅ ጉራጌ ዞኖች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኖቹ 545 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉና ወደ 2ሺህ የሚጠጉ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡


በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ቦጋለ ቢፍቱ፤ የፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን የመልማት ዕድል በመጠቀም ያልተቆራረጠ ልማት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የልማት ዕድሎችን ለመጠቀም ጥያቄዎች ሲነሱ እንደነበር አውስተው መንግስት እያደረገ ባለው ድጋፍ ተገንብቶ የተመረቀው የወልዲያ መስኖ ፕሮጀክት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡


የመስኖ ፕሮጀክቱ በወቅት ሳይገደቡ በዓመት ሶስትና ከዚያ በላይ በማልማት ከራስ አልፈው ለሌላ እንዲተርፉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው በሀድያ ዞን አመካ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ለራጎ መንቾሴ ናቸው፡፡


በወረዳው ድጋፍ የኤልካሜ መስኖ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረግ የግብርና ስራቸውን በአግባቡ እንዲያለሙ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

የመሬትና ውሃ ፀጋን በአግባቡ ለመጠቀም የመስኖ ፕሮጀክቱ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመው ከመኸሩ በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


የአመካ ወረዳ ነዋሪው ርሶ አደር አየለ ኤሪሶ እንደገለፁት፤ አካባቢው ለም መሬት በመሆኑ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የአመካ መስኖ ፕሮጀክት መገንባት ከሚያመርቱት የስንዴና የጤፍ ምርት በተጨማሪ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።


በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ(ዶ/ር)፤ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይም የመስኖ እድሎችን በስፋት የመጠቀም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ስኬት በሀድያና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች 545 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለውና በዞኖቹ ከ1ሺህ 980 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.