የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሐረሪ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ምርታማነትን የማጎልበት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

May 12, 2025

IDOPRESS

ሐረር፤ግንቦት 2/ 2017 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የወተት፣ የዶሮ፣ የማርና የአሳ ምርታማነትን የማጎልበት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር አመለከቱ።


በክልሉ በሌማት ትሩፋት የእንስሳት ሀብት ልማትና ተዋጽኦዎችን ማጎልበት በሚቻልበት ዙሪያ በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።


የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በወቅቱ እንዳሉት፥በሌማት ትሩፋት የወተት፣የዶሮ፣የማርና የአሳ ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።


በተለይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በከተማና በገጠር አርሶ አደሩን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዶሮ፣በወተት ላም እርባታና የንብ ማነብ እንዲሁም በጓሮ አትክልት ልማት ላይ በመሳተፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት እያስቻለ ነው።


ከዚህ በተጨማሪ በሌማት ትሩፋት የሚመረቱ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ህብረተሰቡ ዶሮ፣ ወተት፣እንቁላልና ሌሎች የእንስሳት ተዋጾዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እና የገበያ ዋጋም እንዲረጋጋ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


መድረኩም በከተማው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የወተት፣የዶሮ፣ የማርና የአሳ ምርታማነትን ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችል በመሆኑ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።


ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በዶሮ እርባታ ስራ የተሰማሩት አቶ እስክንድር ደግፌ፤ የክልሉ መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሚያደርገው የድጋፍ ስራዎች ውጤታማ እንዳደረጋቸው ጠቁመው በቀጣይም የመስሪያ ቦታ ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።


ሌላው በከብት እርባታ የተሰማሩት አቶ ከፍያለው ወርቁ፥ ከከብት መኖ ጋር በተያያዘ የሚታዩት ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል።


የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ፤ ከሌማት ትሩፋት ስራዎች ጋር በተያያዘ ከመስሪያ ቦታ፣ ከከብት መኖ አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።


በመድረኩ ላይ በከተማው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በወተት፣ ዶሮ፣ በማርና አሳ ሃብት ልማት ላይ የሚሰሩ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.