የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በመዲናዋ በአራት ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ሆነዋል - አቶ ጃንጥራር አባይ

May 12, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በተከናወነ የንቅናቄ ስራ በአራት ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ፡፡

”ፋይዳ ለኢትዮጵያ” የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።


ውድድሩን ያስጀመሩት አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት በመዲናዋ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተጀመረ ግዜ ጀምሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት ኤጀንሲ አማካኝነት በአራት ወር ውስጥ በተከናወነ የንቅናቄ ተግባር ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በዚሁ ወቅት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተጀመረበት ግዜ ጀምሮ በርካታ ነዋሪዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም ያልተመዘገቡ የከተማዋ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ ለማድረግ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ገልጸው፤ በተለይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቤኔዘር ፈለቀ በበኩላቸው የጎዳና ላይ ውድድሩ በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ንቅናቄ ለመፍጠር ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።


እስካሁን ባለው ሂደት 15 ሚሊዮን የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በመላ ሀገሪቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በተለይ በክልሎች ከአንድ ሺህ በላይ በመሆኑ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ የፋይዳ መታወቂያ አስፈላጊነትን በመረዳት እስካሁን ያልተመዘገቡ ምዝገባ እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውድድሩ አትሌቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስተኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳልያ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷላቸዋል።

በውድድሩ ለተሳተፉ ተወዳዳሪዎችም የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.