አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የሚሰሯቸውን ዘገባዎች ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
ኢትዮጵያ ከቀጣዩ አርብ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ(ETEX 2025)ን ታስተናግዳለች።
ኤክስፖውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹ፤ መገናኛ ብዙሃን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ እያከናወነች ስላለው ተግባራት ጥልቅ መረጃ ማድረስና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው።
አለም አቀፍ ኤክስፖው ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት በአግባቡ ለመረዳትና ለሌሎችም ለማስረዳት ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል።
መንግስት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኤክስፖው ከሌሎች ሀገራት የልምድና የዕውቀት ሽግግር የሚደረግበትና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኤክስፖው የቱሪዝም ዘርፉን የበለጠ ለማስተዋወቅና የሀገርን ገፅታ ለመገንባት የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ፣ ኤክስፖው በተሳታፊ ቁጥርና በቴክኖሎጂ አቅርቦት በአለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያተረፉ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ነው ብለዋል።
በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት መሆኑን ጠቅሰው ኤክስፖው በዚህ ላይ የተሰሩ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ እንደሆነም አንስተዋል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልዕቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ በበኩላቸው፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የሳይበር ደህንነት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ስማርት ሲቲና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ጨምሮ የሮቦቲክስና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውድድሮች ይካሄዳሉ ብለዋል።
በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በተሳታፊ ቁጥር በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑም ታውቋል።
ኤክስፖው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሳይበር ደህንነት ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025