የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው -ቢሮው

May 7, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ ሚያዝያ 28/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ክልል አቀፍ የቡና ተከላ ዘመቻ ዛሬ ተካሄዷል።


ዘመቻውም በወረዳው ቱማታ ጭራቻ ቀበሌ ከ36 ሄክታር በሚልቅ ማሳ ላይ ተከናውኗል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ከ228 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ተሸፍኗል።

በእርጅናና በበሽታ ምክንያት የሚከሰትን የቡና ምርትና ጥራት መቀነስ ለመከላከል በኩታ ገጠም የግብርና ስነ-ዘዴ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን የመትከል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


"በዚህም የቡና ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ብቻ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

ለዚህም ከ37 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ የተከላ ሥራ መጀመሩንና አርሶ አደሩም በኩታ ገጠም ተደራጅቶ 1 ሺህ 400 ሄክታር መሬት እያለማ መሆኑን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ መዳበሪያ አጠቃቀሙን በማሳደግና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመጠቀም የቡና ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

በዞኑ ከ11 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተከላ ለማከናወን ታቅዶ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ብቻ 87 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።


በዞኑ ያረጀ ቡናን በአዲስ ለመተካት የአምስት ዓመት ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ያሉት አስተዳዳሪው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ11 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የቡና እድሳት ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

በተለይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት የቡና ምርታማነት ፓኬጆችን እንዲተገብር መደረጉን ተከትሎ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ጪጩ በበኩላቸው እሳቸውን ጨምሮ 53 አርሶ አደሮች ከ36 ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የነበረን ያረጀ ቡና በማንሳት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቡናን በዘመናዊ መንገድ በመስመር ማልማት ያለመዱት አሰራር መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ማርቆስ ሳሊ ናቸው።

ያረጀ የቡና ዛፍን በመንቀል ከ1 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን መትከላቸውን አስረድተዋል።

በዘመቻው የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.