የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ በመኸሩ የምርት ዘመን ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዷል

May 6, 2025

IDOPRESS

ደሴ፤ሚያዚያ 27/2017(ኢዜአ )፦በደቡብ ወሎ ዞን በ2017/18 የመኸር ምርት ዘመን ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የደቡብ ወሎ ዞን የግብርና መምሪያ የ2017/18 ዓ/ም የምርት ዘመን የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ አካሄዷል።


በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ፤በምርት ዘመኑ ከ432 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የማልማት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ጭምር የሚቀርብ ምርት የማምረት እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም፣በኩታገጠም በማረስና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል በምርት ዘመኑ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በበኩላቸው፣ በዞኑ ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን አረጋግጦ ምርትን በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እንዲችል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


በተለይ በ2017/18 ዓ.ም የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለማምረት ግብዓትን ቀድሞ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በምርት ዘመኑ ከ40 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የጃማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀይሉ አሰፋ ናቸው።

ለዚህም የእርሻ ስራን በትራክተሮች እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፥ ግብዓትም ቀድሞ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው ብለዋል።

የቃሉ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ኢብራሂም በበኩላቸው፥ በወረዳው ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ791 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርታማነትን ለመጨመር ከአርሶ አደሮች ጋር መግባባት መፈጠሩን ገልፀው፥ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አክለዋል።

በመድረኩም የዞን፣የወረዳና የከተማ አመራር አባላት፣ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.