የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት ሊጀመር ነው

Apr 27, 2025

IDOPRESS

ጎንደር፤ሚያዚያ 18/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ለመሳብ በተመረጡ ስድስት ዋና ዋና ከተሞች የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት እንደሚጀመር የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡


ቢሮው ያለፉትን ዘጠኝ ወራት የኢንቨስትመንት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡


በመድረኩ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዮሃንስ አማረ እንደተናገሩት፤ የአንድ ማእከል አገለግሎቱ በክልሉ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከውጣ ውረድ ነጻ የሆነ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡


ማዕከሉ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች በመሰረታዊነት ለመፍታት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የክልሉን ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳለጥ ትልቅ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡


የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ የሚጀመርባቸውም ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ወልዲያ ከተሞች እንደሆኑም አስታውቀዋል።


በማዕከላቱ የኢንቨስትመንት ቢሮን ጨምሮ የመሬት አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት ንግድና ገበያ ልማት እንዲሁም ገቢዎች ቢሮ በጋራ ሆነው በአንድ ቦታ ባለሀብቱ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡


በከተሞቹ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል የአሰራር ደንቦች ተዘጋጅተው መጽደቃቸውን ጠቁመው፤ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው አገልግሎቱን በከተሞቹ ለመጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡


በከተሞቹ አገልግሎቱን የሚሰጡ የባለሙያዎች ምደባም በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተው፥ በቀጣይም አሰራሩን ወደ ሌሎች ከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡


የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጡ ወረቀት አልባ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራርን የሚከተል ሲሆን ባለሀብቶች በየትኛውም ቦታ ሆነው አገልግሎቱን በኦን ላይን እንዲያገኙ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡


የአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ የባለሀብቱን ጊዜና ወጪ የሚቀንስ ነው ያሉት በጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ፋሲል ዘውዱ ናቸው፡፡


የከተማውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ከማሳደግና ቀልጣፋና ዘመናዊ የአገልግሎት የአሰጣጥ ስርአት ከማስፈን አኳያ ማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተው፤ መምሪያው አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 269 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለአንድ ሺህ 898 ፕሮጀክቶች ኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.