ደብረ ማርቆስ፤ሚያዚያ 18/2017 (ኢዜአ) ፡- ምርታማነትን ለማሳደግ በግብአትነት የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀማቸው ወጪን ለመቀነስ ያገዛቸው መሆኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ ለመጪው የመኸር ወቅት በግብአትነት የሚውል ከ35 ሚሊየን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የግብርና መምሪያ አስታወቋል።
አርሶ አደር አጅጉ ታደለ በዞኑ ጎዛምን ወረዳ የገራሞ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት በማሳቸው ለሚለሙት ሰብል ሲጠቀሙ እንደቆዩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።
ይህም ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር በፊት ያገኙት ከነበረው ምርት በሄክታር ከስምንት ኩንታል በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ያስገኘላቸው ውጤት ከዘመናዊው ማዳበሪያ የልተናነሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋትም ዘንድሮ ከ50 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ ወረዳ የጥጃን ቀበሌ አርሶ አደር መለሰ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ከ80 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውም ለዘመናዊ ማዳበሪያ በየዓመቱ የሚያወጡት ወጪ በግማሽ ያህል መቀነስ እንዳስቻላቸው አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሱን ለማስቻል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እምቢያለ አለኸኝ ገልጸዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በግብአትነት የሚውል እስካሁን ከ35 ሚሊየን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ተሳትፎ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለመበተን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁንም ከ80 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ በተካሄደው የመበተንና ከአፈሩ ጋር የማዋሃድ ስራ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል።
ቡድን መሪው እንዳሉት፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም የመሬቱ እርጥበትን የመያዝና ለረጅም ጊዜ ምርት የመስጠት አቅሙ እንዲያድግ የሚያስችል በመሆኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017/ 2018 የምርት ዘመን የአፈር ለምነትን በማሳደግና ሌሎች ተክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን መምሪያው አመላክቷል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025