የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው

Apr 23, 2025

IDOPRESS

ጎንደር፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች ከ110 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡


የመምሪያው ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

እስካሁን በተደረገው የስርጭትና የማጓጓዝ ስራም ወደ መጋዘን ከገባው 139 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 110ሺህ የሚሆነው የአቅርቦት ስራው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስርጭቱም በዞኑ ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎችና በክረምቱ ዝናብ ለተሸከርካሪ አመቺ ያልሆነ መንገድ ባለባቸው ወረዳዎች ላይ በማተኮር ማካሄድ መቻሉን ገልጸዋል።


በመጪው የምርት ዘመን ለማቅረብ የታቀደውን 620 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ በማድረግ አርሶ አደሩ የግብርና ስራውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲያከናውን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለስርጭቱ መሳለጥም በዞኑ የሰፈነው ሰላም የአርሶ አደሩ የእርሻ ስራ ሳይስተጓጎል በወቅቱ የአፈር ማዳበሪያን ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ለአርሶ አደሩ ምርት መቀነስ ምክንያት የሆነውን ህገወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውርና ሽያጭን ለመቆጣጠርም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡


ማዳበሪያ ከጅቡቲ በማጓጓዝ በተዘጋጁ መጋዘኖች ማከማቸትና ወደ ወረዳዎች የማድረስ ስራው በፍጥነት እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ የጸሃይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ይሁኔ ዳኘው ናቸው፡፡

ዩንየኑ በዞኑ 15 ወረዳዎች በተዘጋጁ መጋዘኖች 167 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አጓጉዞ በማድረስ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መሳፍንት በሪሁን እንዳሉት ቀድሞ ለሚዘሩት የበቆሎና የዳጉሳ ሰብል የሚውል ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ በመግዛት ተረጋግተው ለዘር ስራ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሽመልስ ገበያው በበኩላቸው በአካባቢያቸው የሰፈነው ሰላም ማዳበሪያ በወቅቱ አግኝተው የእርሻ ስራ እንዲጀምሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.