የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በትግራይ ክልል በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛው ዙር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጀመረ

Apr 15, 2025

IDOPRESS

መቀሌ፤፤ ሚያዚያ 6/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን በስራ በማሳተፍ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሁለተኛው ዙር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዛሬ በመቀሌ ከተማ መጀመሩ ተገለፀ።

የፌዴራል መንግስት በመደበው ከ670 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ወደ ተግባር የገባው ፕሮግራሙ በተለያዩ የከተማ ጽዳትና ውበት ስራዎች ላይ የሚሳተፉ 3ሺህ 447 የቤተሰብ መሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የፕሮግራሙ መጀመርን አስመልክተው የመቀሌ ከተማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተሻለ ብርሃነ እንዳሉት፤ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች እያዳንዳቸው ቢያንስ አራት ቤተሰቦችን የሚያስተዳድሩ ናቸው።


የሁለተኛው ዙር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ዓላማም ተጠቃሚዎችን ለሶስት ዓመታት በተለያዩ ስራዎች ላይ በማሳተፍ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ወደሚያገኙበት የስራ ሁኔታ እንዲሸጋገሩ ማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የነበሩ 3ሺህ 215 የቤተሰብ መሪዎች በቀጣዩ ወር እንደሚመረቁ አስተባባሪው ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግስት ለመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከ670 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስረድተዋል።

በፕሮግራሙ ተሳታፊ ከሆኑ የቤተሰብ መሪዎች መካከል ወይዘሮ አዝመሩ ካሳ እንዳሉት እስከ አሁን በቀን ስራ እየተንቀሳቀሱ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።

ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚሳተፉበት የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸው ወደ ተሻለ ህይወት ለመሸጋገር እንደመደላድል እንደሚጠቅማቸው ተናግረዋል።

ሰርቶ በመለወጥ ወደ ተሻለ ስራ ለመሸጋገር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራው መልካም አጋጣሚ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወጣት ተክላይ ሀይላይ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.