የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ዳያስፖራው በህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሳተፍበት የኦን ላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ይፋ ሆነ

Apr 11, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚሳተፉበት ፈጣን የኦንላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ይፋ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ እና የፋስት ፔይ ኢቲ (Fastpay-et) መስራች ፍጹም ተስፋዬ የኦን ላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

አምባሳደር ፍጹም በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡

በዚህም ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ልማት፣ በህዳሴ ግድብና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።


የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እስከ መንግስታቱ ድርጅት ድረስ ግፊት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከ አሁን 1 ነጠብ 5 ቢሊዮን ብር በቦንድና በስጦታ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያውያን ተጀምሮ በኢትዮጵያውያን በሚጠናቀቀው ግድብ ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እስከ መጪው ሰኔ ወር 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ገልጸው፤ እስከ አሁን ከ700 ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዘመኑ ዓድዋ ነው ያሉት አምባሳደር ፍጹም ለዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በግድቡ ግንባታ ተሳትፎ የሚያደርጉበት በቴክኖሎጂ የታገዘ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ተዘርግቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሞባይል ስልካቸው በቤታቸው ሆነው ተጨማሪ የመላኪያ ክፍያ ሳይፈጽሙ በቀላሉ ማገዝ የሚችሉበት ዘዴ በመሆኑ ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

የ 'Fastpay .et' ዲጂታል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ መሥራች ፍጹም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓቱ ዳያስፖራው በህዳሴው ግድብ የመጨረሻ ምዕራፍ ግንባታ ላይ ዕድሉን መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ዳያስፖራ የሀገሩ አምባሳደር መሆኑን ገልጸው፤ ዲያስፖራው በመደበኛው የፋይናንስ ስርዓት ተጠቅሞ የሀገሩን ሪሚታንስ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዳያስፖራው ከሚለከው ገንዘብ (ሪሚታንስ) ማግኘት ሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያለንን አቅም በትብብር ሥራ ላይ ማዋል ይገባናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.