ባህር ዳር፤ መጋቢት 30/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የገበያ ትስስር መፈጠሩን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የገበያ ልማት ባለሙያ አቶ መኳንንት እማኘ ለኢዜአ እንደገለፁት ለኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትሰስር መፍጠር የተቻለው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ እድሎችን በመጠቀም ነው።
በዚህም ለ23ሺህ 119 ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር መፈጠሩን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ በውጭ ሀገራት ትስስር የተፈጠረላቸው 62 ኢንተርፕራይዞች 319ሺህ 609 የአሜሪካ ዶላር አስገኝተዋል ብለዋል።
ትስስሩን መፍጠር የተቻለውም በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በኮንስትራክሽን፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በባህላዊ ጌጣጌጥና አልባሳት እንዲሁም በሌሎች የግብርና ውጤቶች መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በግብርናው ዘርፍ በእንስሳት ውጤቶችና ሌሎች የግብርና ምርቶች ትስስር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የገበያ ትስስር ከከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር እርስ በርስ ጭምር መሆኑንም አመልክተዋል።
በደሴ ከተማ የቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዳዊት ጌቱ በሰጠው አስተያየት ሶስት ሆነው በመደራጀት ያገለገሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን ፈጭተው ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል።
መንግስት ባመቻቸላቸው ቦታና ከ700ሺህ ብር በላይ ብድር የፕላስቲክ መፍጫ ማሽን ገዝተው ወደ ስራ በመግባት በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች ክልሎች ምርታቸውን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድቷል።
በዚህም በ350ሺህ ብር የጀመሩት ሥራ አሁን ላይ ካፒታላቸውን ሶስት ሚሊዮን ብር ማድረስ እንደቻሉም አስታውቀዋል፡፡
በ60ሺህ ብር የጀመሩት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ስራ አሁን ላይ ካፒታላቸውን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ማድረሳቸውን የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ መሀመድ ናቸው።
በባዛሮችና በንግድ ትርዒቶች በሚፈጠርላቸው የገበያ ትስስር ምርታቸውን በማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ወጣቶችን በልብስ ስፌት በማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በውጭና በሀገር ውስጥ የገበያ ትስስር የማመቻቸቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025