የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች የንብ ማነብ ሥራን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ ላይ ይገኛሉ

Apr 8, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር ፤ መጋቢት 29/2017 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች የንብ ማነብ ሥራን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የንብና ሃር ልማት ባለሙያ አቶ ሙሀመድ ጌታሁን፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርና የአረንጓዴ አሻራ ለንብ ማነብ ስራ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 31ሺህ 531 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ በተደረገ ጥረት በዘጠኝ ወር ውስጥ ብቻ 25 ሺህ 500 ቶን ማር በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።


የተመረተው የማር ምርት ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 82 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቁመው፤ ቀሪውን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እስካሁን የተመረተው የማር ምርትም ከባለፈው ዓመት አጠቃላይ ምርት ጋር ሲነጻጸር የአምስት ሺህ ቶን ብልጫ እንዳለው አውስተው፤ የዘንድሮው ምርት ባለፉት አስር ዓመታት ተገኝቶ የማይታወቅ ነው ብለዋል።

ለተገኘው ስኬትም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሁም በሌማት ትሩፋት ለአናቢዎች ስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።


ምርቱን ለማሳደግም 500 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደርና ወጣት አናቢዎችን በማሳተፍ በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዘመናዊና ባህላዊ የንብ ቀፎ ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የማር ምርቱን ጥራት በማሳደግ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠርና የማነቢያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ክልሉ በዘርፉ ያለውን ጸጋ ለመጠቀም በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአዊ ብሔረሰብ ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የጅባይታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ስለሽ አረጋ በሰጡት አስተያየት፤ የሌማት ትሩፉት መረሐ-ግብር የንብ ማነብ ስራውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

በ220 ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎች ያመረቱትን ማር በመሸጥ በባለፈው ዓመት 900ሺህ ብር ከማር ሽያጭ ማግኘታቸውን አውስተዋል።

ዘንድሮ ለንብ ማነብ ሥራ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከማር ምርት ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ አንድ ሚሊየን ብር ለማድረስ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን አዋባል ወረዳ ዳበና ቀበሌ “የቁሜ፣ ጤናውና ጓደኞቻቸው ንብ ማነብ ማህበር" ስራ አስኪያጅ ወጣት ቁሜ የኔውድ እንዳለው ፤ የሌማት ትሩፍት መርሃ-ግብር የማር ምርት እንዲጨምር አስችሏል።

ዘጠኝ ሆነው በንብ ማነብ ስራ በመሰማራት ካሏቸው 31 ዘመናዊ ቀፎዎች 600 ኪሎ ግራም ማር ለመሰብሰብ አቅደው ባደረጉት ጥረት እስካሁን 400 ኪሎ ግራም አምርተው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።

በአማራ ክልል ባለፈው የበጀት ዓመት 20 ሺህ ቶን የማር ማርት መገኘቱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.