ሀዋሳ መጋቢት 9/2017 (ኢዜአ) :- ልማታዊ የከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም በሲዳማ ክልል ከተሞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት በመቀየር ከተረጂነት እንዲላቀቁ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገለጹ።
በሀዋሳ ከተማ 13 ሺህ 552 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስጀመሪያና ማስመረቂያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ድህነትን ለመቀነስና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ለመደገፍ የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
በክልሉ ከተሞች እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት በመቀየር ከተረጂነት እንዲላቀቁና ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ አድርጓል ብለዋል።
በፕሮግራሙ ታቅፈው ሀብት ያፈሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ በበኩላቸው በክልሉ በሀዋሳና በይርጋለም ከተሞች በሚተገበረው ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ23 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ በከተሞች የሚታየውን ስራ አጥነትና ድህነት ከመቀነስ ባለፈ ዜጎች ከተሞች ከሚያመነጩት ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ልማታዊ የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት በፕሮግራሙ የታቀፉ ከ9ሺ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ከተረጂነት መውጣት የሚያስችላቸውን አቅም ፈጥረው መመረቃቸውን ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ክፍሎቹ በቆጠቡት ገንዘብና ከመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም እንዲሸጋገሩ ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በከተማው የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የሚደግፉ ፓኬጆች መቀረጻቸውንም ተናግረዋል።
13 ሺህ 552 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ዛሬ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል የምግብ ዋስትናና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሽታ ኤቢሶ ናቸው።
በፕሮግራሙ የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎችም በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በፅዳት፣ በአረንጓዴ ልማትና ውበት፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ በከተማ ግብርናና በአነስተኛ የመሰረተ ልማት ስራዎች በማሳተፍ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ይደረጋል ብለዋል።
በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ከታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች 2 ሺህ168 የሚሆኑት በቀጥታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩም በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የተገነቡ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተመረቁ ሲሆን ውጤታማ ለሆኑ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎችም ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።
አዲስ አበባ ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች ፋይዳ መታወቂያን ተጠቅመው በዲጂታል አማራጭ ትኬት የሚቆርጡበት አሰራር ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የለማ የትራንስፖርት ኦፕሬተሮችንና የጭነት ባለቤቶችን የሚገናኝ መተግበሪያ አስጀምሯል። ...
Feb 12, 2025