የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በጎንደር ከተማ በእድገት ተኮር የስራ ዘርፎች ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል

Mar 13, 2025

IDOPRESS

ጎንደር፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ ባለፉት ስምንት ወራት በእድገት ተኮር የስራ ዘርፎች ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ስራና ስልጠና መምሪያ አስታወቀ።

በከተማው የተቋቋመው የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት የስራ እድል ፈጠራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።


በግምገማው መድረክ የተገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ፤ በከተማው በፌዴራልና በክልሉ መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችም በርካታ ወጣቶችን በስራ እድል ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የከተማውን ጸጋዎች በጥናት በመለየት ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

የብድር የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ችግሮችን በመፍታት በኩል ከተማ አስተዳደሩ ለሼዶች ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ስራና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ ላቂያው አንዳርጌ፤የስራ እድሉን መፍጠር የተቻለው በበሌማት ትሩፋት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎች የእድገት ተኮር ዘርፎች ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማው በሚካሄዱ የኮሪደር ልማትና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት የእድሳትና ጥገና ስራዎችም በርካታ ስራ አጥ ወገኖች ጊዚያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ700 በላይ አዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉም ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር እንዳስቻለ አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩም ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ለ108 ነባርና አዲስ ኢንተርፕራይዞች ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት መቻሉን አስታውቀዋል።

የመሸጫና የማምረቻ ቦታ ችግርን ለመቅረፍ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሼዶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ግንባታው እንደተጠናቀቀ ለኢንተርፕራይዞች ይሰራጫል ብለዋል።

በቀሪ ወራትም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ከዚህ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ለምክር ቤቱ አረጋግጠዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን ጨምሮ የስራና ስልጠና መምሪያው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.