የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)</p>

Jan 22, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ነው።

ኢንተርኔት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለማህበራዊ ትስስርና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው፥ ለቀጣናዊ ትብብርና ለፈጠራ ማደግ ምቹ ምህዳር የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

ሆኖም በቀጣናው ካለው ፍላጎት አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት አሁንም ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ መሰረት የዲጂታል ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰዋል።


የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፋችና እያዘመነች መሆኑን ገልጸው የ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት ሀገራዊ ሽፋን 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።

5ጂ ኔትወርክም በትላልቅ ከተሞች አገልግሎት መጀመሩንና ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ነው ያሉት።

ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው ቴሌ ብር ከ51 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮችና የዳታ ማዕከል አቅራቢዎች በሀገሪቱ እንዲሰማሩ በማድረግ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ አገልግሎትና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትና በአፍሪካ የዲጂታል አብዮት መሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለሦስት ቀናት የሚቆየው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.