የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

<p>በክልሉ እየተከናወነ ያለው የመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ከማጎልበት ባለፈ ገበያን እያረጋጋ ነው</p>

Jan 21, 2025

IDOPRESS

ሐረር፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ከማጎልበት ባለፈ ገበያን እያረጋጋ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በመስኖ ልማቱ የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮው በጋ ወራት 4ሺህ 700 ሄክታር መሬት ልዩ ልዩ አትክልትና ፍራፍሬ በመስኖ እየለማ ነው።


በዓመት ሶስት ጊዜ ለማምረት በሚከናወነው የመስኖ ልማት የመጀመሪያ ዙር የምርት መሰብሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ አስፈላጊው የምርት ግብዓት ቀርቦለት ምርትና ምርታማነትን የማጎልበት ስራ በተጠናከረ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለከተማው ማህበረሰብ በማቅረብ የዋጋ ማረጋጋት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ለልማት ሰራተኞችና ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት የምርት ግብዓት በማሟላት የመስኖ ልማቱ በተያዘው እቅድ እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ደግሞ በክልሉ የሶፊ ወረዳ ግብርና ልማት አስተባባሪ አቶ ጃፈር ከዲር ናቸው።

በወረዳው የሚከናወነው የግብርና ልማት ስራ ተረጂነትን ለመቀነስ እያገዘ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ ከመስኖ ልማቱ 200 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።


ዘንድሮ ለመስኖ የሚያስፈልጉ ሁሉም አቅርቦቶች በተሻለ መልኩ በመከናወናቸው እና የግብርና ባለሙያዎች እገዛ ከፍተኛ በመሆኑ የተሻለ ምርት ማምረት ችያለሁ ያሉት ደግሞ በክልሉ ሶፊ ወረዳ አርሶ አደር መጂድ አብዱላሂ ናቸው።

ወጣት አርሶ አደር ሙራድ መጂድ በበኩሉ ቀደም ሲል በቆሎ እናመርት ነበር፤ በመስኖ ሽንኩርት ማልማት እንደምንችል የግብርና ባለሙያዎች በመከሩን መሰረት አምና ካመረትነው የሽንኩርት ልማት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችለናል ብሏል።


ዘንድሮም ከ400 ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙም አርሶ አደሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.